የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚኖረውን ሚና በውል ተረድቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

269

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር የሰው ሰራሽ አስተውሎት በውጭ ግንኙነት እና በደህንነት ላይ ያለውን ሚና በውል ተረድቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

በውጪ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት "ዓለም አቀፋዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር ስርዓት ጅምሮች እና የኢትዮጵያ ትልም" በሚል መሪ ሀሳብ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን ዓለማየሁ፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ተገኝተዋል።

የመድረኩ ዓላማም የሰው ሰራሽ አስተውሎት በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ተልእኮ ላይ ያለውን ጠቀሜታ እና ተጽእኖ ማስገንዘብ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ መስኮች የዓለምን አሰላለፍ እየቀየረ ነው።

ቀደም ካሉ የቴክኖሎጂ አብዮቶች የላቀ ውጤት እንደሚያመጣ የታመነበት መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የአገራት የበላይነት እና ተከታይነት አይቀሬ መሆኑ እየታየ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በአገራት መካከል በጉዳዩ ላይ ድርድሮች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አፍሪካ በዓለም መድረክ ጥቅሟን እንድታስከብር እንደ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን አጀንዳ ቀደም ብለው ያነሱ አገራት የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ እኳያ እንደ ሀገር ሊኖር ስለሚገባው ዝግጅት እና መያዝ ስላለበት አቋም በጥናት ላይ የተመሰረተ አካሄድን መቅረጽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በውጭ ግንኙነት እና በደህንነት ላይ ያለውን ሚና በውል ተረድቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በምህዳሩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ቴክኖሎጂውን መከታተል እና የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል  ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ  መዳበር የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።


 

 በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሀገሪቱ የውጪ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ እንዲዳብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአስተዳደር ስርዓቱም ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂን ለተለያዩ አገልግሎቶች በመጠቀም ላይ እንደምትገኝ ገልጸው ቴክኖሎጂውን በመረዳት የሚመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ  መቆጣጠር እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ነው ያሉት ደግሞ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን ዓለማየሁ ናቸው።


 

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸው፥ ይህም የዲጂታል ስነ ምህዳሩ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዲጂታል ሽግግርን ለማሳለጥ ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ጥቅም ላይ ሲውል በማስተዋል እና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲያድግ እንዲሁም ኃላፊነት የተሞላበት አጠቃቀም እንዲኖር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም