ለጸሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ለጸሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦ ለጸሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ የክብር ዲፕሎማና እውቅና ተሰጠ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ 3ኛ አመታዊ የሥነ ጥበባት ዝክር በሀገር ፍቅር ቴአትር አካሂዷል።
በመርሐ ግበሩ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ባለፋት ሁለት ዓመታት ለአርቲስት አብራር አብዶና ለአርቲስት ዳዊት ይፍሩ እውቅና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡
የዘድሮውን በድንቅ የተውኔት ስራው ለዘመናት ትውልድ በማነጽ፣ ሙያውን አክብሮ ከማስከበሩም በላይ የበርካታ ስራዎች ባለቤት ለሆነው ውድነህ ክፍሌ ማበርከቱን አስታውቀዋል።
የጸሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ስራዎች ለትውልድ እየተላለፉ ለምርምርና ለመማሪያ የሚያገለግሉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከውድነህ ክፍሌ ከደረሳቸው የተውኔት ስራዎች መካከል ግማሽ ጨረቃ፣ የደፈረሱ ዓይኖች፣ ባቢሎን በሳሎን፣ በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ፣ ቅጥልጥል ኮከቦች፣ የለሊት ሙሽሮችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።