ቁልፍ ለሆኑ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ እየተደረገ ነው

298

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦ ቁልፍ ለሆኑ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ሳይበር ደኅንነት ማኅበር ጋር ያዘጋጁት የሳይበር ደኅንነትና ዲጂታል ሽግግር ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ብሎም ሀገራዊ የሳይበር ሥነ-ምህዳር ለማጠናከር ኮንፍረንሱ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ ተቋሙ ቁልፍ የሆኑ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማትን የሳይበር ደኅንነት የማስጠበቅ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም ትላልቅና ወሳኝ የሆኑ መሠረተ-ልማቶችን፣ የፋይናንስና የሚዲያ ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ በንቃት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የሳይበር ጥቃት መነሻዎች የተለያዩ ቦታዎች መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ የመከላከሉ ሥራም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የሳይበር ደኅንነትን በተመለከተ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ፤ የ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማስተግበር በዘመናዊ የዲጂታል ሽግግር የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የሳይበር ሥርዓቱን ደኅንነት ማስጠበቅ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማትና ግለሰቦችም የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይበር ደኅንነት ማኅበር እየሰራ ላለው በጎ ተግባር ሚኒስቴሩ የሚደግፈውና የሚያበረታታው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ በየነ፤ ጉባዔው የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ብሎም ሀገራዊ የሳይበር ሥነ-ምህዳርን ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ የሳይበር ደኅንነት፣ የሳይበር ሕግ እና ተያያዥ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ከ12 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶችና ተጋላጭነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከተሰነዘሩ 4ሺህ 623 የሳይበር ጥቃቶች 98 በመቶውን ማክሸፍ መቻሉ ይታወቃል።

የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት በአጠቃላይ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም