ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቶች የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት ናቸው-አምባሳደር መስፍን ቸርነት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አትሌቶች የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት መሆናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።

በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክሱ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እና በስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድኖች የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም መድረኮች የአገራቸውን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው የሚያስጠሩ ናቸው።

በቱኒዚያና ስኮትላንድ የተመዘገቡት ውጤቶች አትሌቶች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው አገር የሰጠቻቸውን አደራ መወጣት እንደሚችሉ ያሳዩ  ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ አትሌቶች የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

በቀጣይ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተፎካካሪዎች በልጦ ለመገኘትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ  እንደሚገባም ገልጸዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ በቀጣይ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስፖርታዊ መድረኮች የተሻለ ውጤት እንድታገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሮቹ አመርቂ ውጤት በማስመዝገባችሁ ኢትዮጵያ ኮርታባችኋለች ብለዋል።

ውጤቶቹ አበረታች ቢሆኑም  በፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችና በቀጣይ በሚከናወኑ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ብዙ መስራት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስ ስፖርት ለመሳተፍ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው በውድድሮቹ ላይ የተገኙት ወጤቶች በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል።

ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለአትሌቲክሱ ስፖርት እድገት ድጋፉን ማድረግ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ለልዑካን ቡድኑ አባላት በአጠቃላይ ከ800 ሺህ ብር በላይ ሽልማት አበርክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም