በትግራይ ክልል  አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት  ለእርሻ ልማት ግብአት እንዲጠቀሙ  ትኩረት ተሰጥቷል

ማይጨው፤  የካቲት 26 /2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል   አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት  ለእርሻ ልማት ግብአት እንዲጠቀሙ  ትኩረት መሰጠቱን  የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ ገለጹ።

በክልሉ  53 ወረዳዎች ውስጥ ከሚገኙ 214 ቀበሌዎች የተውጣጡ ከሦስት ሺህ በላይ  ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ስልጠና በተለያዩ  ከተሞች እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

የዚሁ አካል የሆነ ስልጠና  በማይጨው ከተማ ተካሄዷል።

ዶክተር ኢያሱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የግብርና ምርትንና የመሬት ለምነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የክልሉ አርሶ አደሮች   የተፈጥሮ ማዳበሪያን  አዘጋጅተው   በግብአትነት እንዲጠቀሙ  ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህም  በክልሉ የሚገኙ ከ243 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በዘመናዊ መልኩ በሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ጨብጠው  እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

ስልጠናው አርሶ አደሩ  ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ከመጠቀም በተጨማሪ የግብርና ምርትን በዘላቂነት ለማሳደግ በአካባቢው ከሚገኙ ተረፈ ምርት  የተፈጥሮ ማዳበሪያን አምርቶ ለመጠቀም  የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያሳድግለትም አስረድተዋል።

ለሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ ፋይዳው የላቀ መሆኑን  ኃላፊው ተናግረዋል።

የተፈጥሮና ዘመናዊ ማዳበሪያ አጣምረው የተጠቀሙ አርሶ አደሮች እስከ አምስት ኩንታል ምርት ጭማሪ እንዳገኙ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እንደተረጋገጠ ጠቅሰዋል።

ስልጠናው ለሁሉም አርሶ አደሮች ተደራሽ ሲደረግና ተግባራዊ ሲሆን በክልሉ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ  እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የቶፕ የተፈጥሮ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ አምራች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ታደሰ ፤ድርጅቱ ባጠረ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ በሆነ መልኩ የሚዘጋጅ  ተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና አጠቃቀም ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር  ስልጠናውን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።


 

በስልጠናው የተካፈሉት የሳምረ ወረዳ ለምለም ቀበሌ አርሶ አደር ሐበን ሐዱሽ ፤ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢ ከሚገኝ ፍግ፣ አመድ፣ ቅጠላ ቅጠልና ከሌሎችም ግብዓቶች በማዘጋጀት ስጠቀም ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም የአፈር እርጥበትንና ለምነትን ጠብቆ በማቆየት የተሻለ ምርት ለማግኘት እንዳስቻላቸው  አውስተዋል።

አሁን በሚወስዱት ስልጠና ደግሞ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው አመልክተው፤ ከስልጠናው  የሚያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀማቸውንና በዚህም  ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግዢ  ያወጡ የነበረውን ወጪ በግማሽ  መቀነስ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ደግሞ የእምባ አላጄ ወረዳ ዓፀላ ቀበሌ ሴት አርሶአደር  መሰለች ታረቀ ናቸው።

በክልሉ 53 ወረዳዎች ከሚገኙ 214 ቀበሌዎች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ ሞዴል አርሶ አደሮችና አንድ ሺህ የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ስልጠናውን በዙር እንደሚሰጣቸው ተመላክቷል።

በማይጨው ከተማ  የተሰጠው ስልጠና ያዘጋጁት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት(ዩኤስ ኤይድ) እና ቶፕ የተፈጥሮ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ አምራች ድርጅት እንደሆነ ተወስቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም