በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ለቴክኖሎጂ እና አዳዲስ አሰራሮች ትኩረት ተደርጓል -ዶክተር አየለ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ለቴክኖሎጂ እና አዳዲስ አሰራሮች ትኩረት ተደርጓል -ዶክተር አየለ ተሾመ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት ቴክኖሎጂ እና አዳዲስ አሰራሮችን ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ተናገሩ።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው ስምንተኛው አገር አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ ላይ ነው።
ዶክተር አየለ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በጤና ኤክስቴንሽን፣ በወረዳ ሽግግር እና አጠቃላይ የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።
በዚህም የጤና አገልግሎት ጥራት ወደተሻለ ደረጃ ማደጉን ጠቅሰው፥ የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ አበረታች ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የጤና አገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን የታገዘ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል።
ለዚህም በቴሌ ሜዲሲን፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሌሎችም ዲጂታል መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ሚኒስቴሩ የጤና ዘርፍ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራዊ አሰራሮች እንዲመራ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሁሉም መስሪያ ቤቶች ለሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በፖሊሲ የተደገፉ ቴክኖሎጂ መር ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በጉባኤው ላይ የፌዴራል እና የክልል ጤናው ዘርፍ አመራሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችና ለጋሾች እንዲሁም የጥናትና ምርምር ተቋማት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የጤና ኢኖቬሽን እና ጥራት ጉባኤ ከየካቲት 26 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይመክራል።
በጤና መስክ እየተተገበሩ ያሉ የለውጥ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ላይ በሰፊው ውይይት እንደሚደረግም ተመላክቷል።
በጉባኤው ላይ ከ650 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን በጤናው መስክ የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቃኝ አውደ ርይዕም ተከፍቷል።