በድላችን ሐውልት ክላሽንኮቭ መሳሪያ ይዘው ሐውልት የተቀረጸላቸው የካራማራው ዘማች አቶ በቀለ ገመቹ 

አቶ በቀለ ገመቹ ወይም በቅፅል ስማቸው አሚኮ ይባላሉ፤ በሙያቸው ኤሌክትሪሺያን ናቸው።

በ1969 ዓ.ም በዚያድባሬ የሚመራው የሶማሊያ አገዛዝ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ሀገር ስትደፈር ቁጭት ተሰምቷቸው ወደ ጦር ሜዳ መዝመታቸውን ይናገራሉ።

ጦር ሜዳ ከመዝመታቸው ባሻገር የኤሌክትሪክ ባለሙያ በመሆናቸው "በራ በራ የድል ጮራ" የተሰኘውን ዓርማ በመቅረጽ በ14ቱ ክፍላተ ሀገር እንዲበራ ማድረጋቸውንም ያነሳሉ።

በዚህም ከወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ከኩባው ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ መሸለማችውን ያወሳሉ።

ታንክ ማራኪው አሊ በርኬ ጓደኛቸው እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ በቀለ፤ በተለያዩ ዐውደ ግንባሮች መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።

አቶ በቀለ ጥቁር አንበሳ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በሚገኘው የድላችን ሐውልት ላይ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ይዘው ሐውልት ተቀርጾላቸዋል።

ሐውልት እንዲቀረጽ የተደረገበት ፎቶግራፍ በያኔው ሶስተኛው አንበሳው ክፍለ ጦር በኋለኛው ምሰራቅ ዕዝ በር ላይ በቀኝ እጃቸው መሳሪያ ከፍ አድርገው ይዘው የተነሱት ፎቶ ግራፍ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።

ከእርሳቸው ጎንም መንበረ የምትባል ሌላ ኢትዮጵያዊ ዘማችና መትረጊስ ተኳሽ ሴት ባደረገችው አስተዋፅኦና በደረሰባት አካል ጉዳት ሐውልት እንደተቀረጸላት ያነሳሉ።

የካራማራ ድል ታላቅ ድል ነው የሚሉት አቶ በቀለ ገመቹ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለውበት የተገኘና ሀገርን ያስከበረ መሆኑንም ይገልጻሉ።

የካራማራ ዘማቹ አቶ በቀለ ገመቹ አሁናዊ ኑሯቸው ችግር ላይ እንደሚገኙና ድጋፍ እንደሚሹም ተናግረዋል።

ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ዚያድባሬ 'ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት' በሚል "ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል" እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው የሚታወስ ነው። 

ይሄን እውን ለማድረግ በ1969 በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ፈጸሙ።

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድል አደረገ፤  የኢትዮጵያ አሸናፊነትም በአደባባይ ታወጀ።

ድሉ በየዓመቱ የካቲት 26 ቀን የሚታሰብ ሲሆን ዘንድሮም 46ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም