ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ዴንማርክ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራሉ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ዴንማርክ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውንና በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተውን የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዴንማርክ ፓርላማ የውጭ ፖሊሲ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይቷል።

የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት ዘርፎች እየተከናወነ ያለውን የለውጥ ሥራ አብራርተዋል።

ጎን ለጎንም ወቅታዊ የአገሪቱን የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በተለይም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በፕሪቶሪያው የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ትግበራ አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን  በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያከናውናቸውን ተግባራትም ዘርዝረዋል።

በሂደት ላይ ያለው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል። 


 

በፖለቲካ ሊሂቃንና የኃሳብ መሪዎች መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።  

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ሶማሊያ ያላትን የሰላም አስተዋጽኦ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል። 

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር የምጣኔ ኃብት፣ የመሰረተ ልማት፣ የንግድና ሌሎች ዘርፎች ትስስር ለመፍጠርም በትኩረት እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብነትም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ የተገነባውን የታላቁ የሕዳሴ ግድብን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ሥምምነት ለቀጣናው ሠላምና ደኅንነት እንዲሁም ምጣኔ ኃብት እድገት ያለውን አስተዋጽዖም አብራርተዋል።


 

የዴንማርክ ፓርላማ የውጭ ፖሊሲ ኮሚቴ ሰብሳቢ ማይክል አስትረፕ በበኩላቸው ኮሚቴው በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅና የአገራቱን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልባቸው ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ በአገር ውስጥ ያሉ ችግሮች በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በአድናቆት እንደሚመለከቱት የዴንማርክ ፓርላማ የውጭ ፖሊሲ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የዴንማርክ የፓርላማ ተወካዮች በፓርላማ የሴቶች ተሳትፎና በሌሎች የፓርላማ ግንኙነቶች  ልምድ በመለዋወጥ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። 

ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን በምጣኔ ኃብት፣ በፖለቲካና ማኅበራዊ ዘርፎች የበለጠ በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይም  በስፋት መክረዋል።

 ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውንና በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተውን የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ በመድረኩ ተገልጿል።   

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም