በክልሉ አዳዲስ ባለሃብቶችን ከመሳብ ባለፈ፤ ነባር ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ማምረት እንዲችሉ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ - አቶ እንድሪስ አብዱ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አዳዲስ ባለሃብቶችን ከመሳብ ባለፈ፤ ነባር ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ማምረት እንዲችሉ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ - አቶ እንድሪስ አብዱ
ደብረ ብርሃን፤ የካቲት 25/2016 (ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል አዳዲስ ባለሃብቶችን ከመሳብ ባለፈ፤ ነባር ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ማምረት እንዲችሉ የተጀመሩ ስራዎች የሚጠናከሩ መሆኑን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ገለጹ።
በአማራ ክልል ደረጃ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።
አቶ እንድሪስ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ንቅናቄው በአማራ ክልል የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው።
በንቅናቄው ለረጅም ዓመታት ቆመው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ችግሮቻቸውን በመፍታት ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል።
በዚህም ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ምርቶቻቸውን ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደተቻለ ሃላፊው ተናግረዋል።
በቀጣይም አዳዲስ ባለሃብቶችን ከመሳብ ባለፈ፤ ነባር ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ማምረት እንዲችሉ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሀይወት፣ በከተማዋ በባለሀብቱና በአስተዳደሩ መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በከተማዋ ያሉትን የኢንዱስትሪዎችን ትስስር ለማጠናከር 3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ገልጸው በዚህም ባለሀብቶችም ወደ ምርት የመሸጋገር አቅማቸው ማደጉን አቶ ብርሃን ተናግረዋል።
መድረኩ ችግሮችን በጋራ በመለየት ለቀጣይ የልማት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን መኪና መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ አህመድ፣ መንግሥት ለባለሃብቶች እያደረገ ያለው እገዛ የሚያበረታታ መሆኑን አመልክተው፣ አሁንም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ፋንታሁነኝ በበኩላቸው ተቋሙ በአካባቢው ያለውን የቴሌ መሰረተ ልማት ለማዘመን 210 ሚሊየን ብር መድቦ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ሪጅኑ የሚጠይቀውን የኔትወርክ ማስፋፊያ ቦታ ካቀረቡ የባለሀብቶቹ ጥያቄ በፍጥነት ምላሽ ያገኛልም ብለዋል።