ቀጥታ፡

በህገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀረሪ ክልል አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2016(ኢዜአ)፡- በህገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀረሪ ክልል አስታውቋል።

ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በኢንቨስትመንት ስም ለረጅም አመታት ታጥረው በቆዩ እና ህገ ወጥ ወረራ የተካሄደባቸው መሬቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

ክልሉ ጉዳዩን በማስመልከት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል ፦

ከሀረሪ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በሀረሪ ክልል በህገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

እንደሚታወቀው ህዝባችን በተለያዩ መድረኮች ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ በክልሉ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የቱሪዝም ስፍራዎችና የአርሶ አደር መሬቶች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ህገ ወጥ የቤት ግንባታዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ነው።

ሌላኛው ደግሞ በኢንቨስትመንት ተወስደው ለረጅም ጊዜያት ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታጥረው የቆዩ መሬቶች ላይ አግባብነት ያለው የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በተለይ አንድ አንድ የግል ጥቅማቸውን ያስቀደሙ አካላት የክልሉ ልማት ላይ እንቅፋት በመፍጠር እና የመሬት ደላሎችን በማሰማራት የግል ፍላጎታቸውን ሲያስቀድሙ ተስተውለዋል።

በዚህም እጅግ ውስን በሆነውና በማይተካው የህዝብና የመንግስት የመሬት ሀብት ያልተገባ ጥቅም እያገኙና የህዝቡንና የክልሉን መንግስት እየጎዱ ይገኛሉ።

በዚህም መሰረት ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄዎች ለመፍታት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አግባብ ያላቸው አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገብቷል፣ ስራውም በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበትና ህብረተሰቡን ያሳተፈ በመሆኑ ውጤት እየተገኘበት ይገኛል።

በአብዛኛው የማህበረሰቡ ክፍሎች ህገ-ወጥ ተግባሩ ተገቢ እንዳልነበር በማመን ያለአግባብ የገነቡትና ያጠሩትን በማፍረስ ለህግ ተገዢነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ለዚህም የክልሉ መንግስት ልባዊ ምስጋና ያቀርባል።

በቀጣይም በተለይ መሬት አጥረው የያዙና ህግ ወጥ ግንባታ ያከናወኑ ግለሰቦች በፈቃደኝነት እንዲያፈርሱም የክልሉ መንግስት ጥሪ ያቀርባል።

ለህግ ተገዥ ባልሆኑ ህገ-ወጥ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ የክልሉ መንግስት ለሰላም እና የህግ በላይነት መከበር የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል።

በዚህ አጋጣሚ ለክልሉ የፀጥታ እና የህግ አስከባሪ አካላት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እየፈፀሙት ላለው ተግባር ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብን መላው የክልላችን ህዝብም ለነዚህ አካላት አስፈላጊው እገዛ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት

የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

ሀረር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም