ቀጥታ፡

ፀሐይ ኃይል ማመንጫና በገጠር መንገድ ግንባታ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2016(ኢዜአ)፡- በፀሐይ ኃይል ማመንጫና በገጠር መንገድ ግንባታ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የዞኑ መንገድ መምሪያ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ ወረዳን ከወረዳና ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ የገጠር መንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልጿል።

ለዓመታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነው መቆየታቸውን የሚናገሩት በዞኑ የጃናሞራ ወረዳ ነዋሪዎች፥ አሁን ላይ ጥያቄያቸው መልስ ማግኘቱን ያነሳሉ።

በወረዳው የዋሰል ንዑስ ወረዳ ነዋሪው ምህረት ከፍያለው ለብዙ ዓመታት ስራ አጥ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሶ፥

በአካባቢያቸው የፀሐይ ኃይል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ግን በዳቦ ማምረት ስራ መሰማራቱን ይናገራል።

የፀሐይ ኃይል መሰረተ ልማት ባይገነባ ኖሮ ዳቦ ቤት መክፈት ቀርቶ ማሰብ እንደማይቻል የገለጸው ወጣቱ፥ አሁን ላይ ከጓደኛው ጋር  በተሰማሩበት ስራ ውጤታማ ለመሆን እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

ሌለኛው በጸጉር ማስተካከል ስራ የተሰማራው ወጣት ጤና ማዕረግ ቀደም ሲል ለጀነሬተር ነዳጅ ለመግዛት በወር እስከ 4ሺህ ብር ወጪ ያደርግ እንደነበር ይገልጻል፡፡ 

አሁን ላይ ግን የፀሐይ ኃይል አገልግሎት በመጀመሩ በወር እስከ 300 ብር ብቻ ወጪ እንደሚያደርግ ገልጾ ራሱን ለመለወጥ ጠንክሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዋሰል የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ኤሌክትሮ መካኒክ ቴክንሺያን ኃይሉ አጎናፍር እንዳሉት፤ የገጠር አካባቢዎችን ከጨለማ ማላቀቅን ዓላማ ያደረገው የታዳሽ ኃይል ልማት ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡

ለአብነትም በዋሰል አካባቢ ከ500 በላይ ደንበኞች ብርሃን ከማግኘት ባለፈ መደበኛ የዕለት ከዕለት ስራዎቻቸውን ለማከናወን የሚያስችላቸውን ኃይል እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ መረጃ በዞኑ በገጠር መንገድ ግንባታ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አቶ ቢያይልኝ ውበቱና ወይዘሮ ወለባ ወንድማገኝ፥ ከመካነብርሃን ወረዳ እስከ ዋሰል የ52 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የገጠር መንገድ ስራ በመከናወን ላይ በመሆኑ መደሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በመንገድ ችግር የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናወን አስቸጋሪ ሆኖባቸው መቆየቱን በማንሳት፥ መንግስት ለገጠር መንገድ  የሰጠው ትኩረት ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሰሜን ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን ወርቁ በዞኑ ሶስት የመንገድ ፕሮጀክቶች በክልሉ የገጠር መንገድ ግንባታቸው እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ግንባታቸው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ከበለስ-መካነብርሃን የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በመጪው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም