ኢትዮጵያ በአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ በመሆን አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ በመሆን አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2016 (ኢዜአ)፡- በ19ኛው የአለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
በስኮትላንድ ግላስጎ ሲካሄድ የነበረው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ትናንት ሌሊት ተጠናቋል።
በውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ650 በላይ አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያም በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር እና በ3000 ሜትር ርቀቶች በ8 ሴቶች እና በ5 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ተሳትፋለች ፡፡
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሴቶች 800 ሜትር ፅጌ ዱጉማ እና በሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሀይሉ የወርቅ ሜዳሊያን አሸንፈዋል።
በሴቶች 3000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የብር እንዲሁም በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የነሃስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኙ አትሌቶች መሆናቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ አንድ ነሀስ በአንድ ብር በአጠቃላይ በአራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።