ቀጥታ፡

በደብረ ብርሀን ከተማ በ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተገነቡ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት መሸጋገራቸው ተገለጸ

ደብረ ብርሃን፤ የካቲት 24 /2016(ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተገነቡ 17 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት መሸጋገራቸው ተገለጸ።

በከተማ አስተዳደሩ በባለሃብቶች የተገነቡ አራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዱ ሁሴን፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድና ሌሎች የአመራር አባላት ተገኝተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ብርሀን ገብረህይወት በወቅቱ እንደገለጹት፤ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በከተማው ያለውን የኢንዱስትሪዎች የማምረት እንቅስቃሴ ከፍ እንዲል አስችሏል።

በአስተዳደሩ 10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተገነቡ 17 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው 37 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ኢንዱስትሪዎች ዛሬ ተመርቀው ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

ከተመረቁት ኢንዱስትሪዎች መካከልም ኤም ዲ ኤፍ ማምረቻ፣ ቴክስታይል፣ የምግብ ማቀነባበሪያና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩም ተመልክቷል።


 

በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ስምንት ወራት ከ4 ነጥብ3 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 39 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንና ከ42 ሄክታር በላይ የግንባታ ቦታ መተላለፉን አብራርተዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ ብልሹ አሰራሮችን ለማቃለል በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የማዘጋጃ ቤት አሰራሩን ለማዘመን እንዲቻል ሶፍት ዌር ተዘርግቶ መመረቁን ጠቅሰው፤ ይህም ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ የዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስችል ነው ብለዋል።

የዲጅታል ሶፍት ዌሩ ዝርጋታም ከተማ አስተዳደሩ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መሰራቱን አመልክተው፤ ከ38 ሺህ በላይ ፋይሎች ወደ ዲጂታል የፋይል አደረጃጀት መቀየራቸውን አስታውቀዋል።

የደህንነት ካሜራ በመግጠምም በከተማው የአገልግሎት አሰጣጡ ሂደት ላይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ብለዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ እስካሁን ከ115 ቢሊዮንን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 621 ኢንዱስትሪዎች እንዳሉና ከመካከላቸውም 98ቱ የግንባታ ሂደታቸውን አጠናቀው በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

ለ22 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩም ከከተማው አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም