ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

ሐረር፤የካቲት 24 / 2016 (ኢዜአ)፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲያደርጉ የቆዩቱን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ  በሐረሪ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። 

በክልሉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ዘንድሮ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ  በቦንድ ግዢ  መሰብሰቡን በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት  የህብረተሰብ ክፍሎች ፤  የግድቡ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለ አንስቶ አቅም በፈቀደ መልኩ የቦንድ ግዢ በመፈጸም  አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ጅንኤላ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ  ስራ ከተሰማሩት አባላት መካከል  ወጣት መስፍን ተወልደ እንዳለው፤ የግድቡ  ግንባታ የተሳካ እንዲሆን በራሱ ተነሳሽነት ሲደግፍ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅትም በማህበራቸው በኩል የ30 ሺህ ብር የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ጠቅሶ፤  ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል።

በከተማው የሚገኘው የአውዚን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አንተነህ እሸቱ በበኩላቸው፤ ባለፉት 4 ዓመታት በመረዳጃ ማህበራቸው አማካኝነት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የ20 ሺህ ብር የቦንድ ግዢ መፈፀማቸውን አስታውስዋል።

ዘንድሮም የ10 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ገልጸው፤ በተለይም በትምህርት ቤቱ ውስጥ መምህራንና ተማሪዎችን በማስተባበር  የቦንድ ግዢ እንዲከናወን በቁርጠኝነት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

እድሩ ከተመሰረተ ጀምሮ 25ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ በሸንኮር ወረዳ  የሌማይስራ እድር  አስተባባሪ  ወይዘሮ ነጻነት ታዬ ናቸው።

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ህጻን አዋቂ ሳይባል ሁሉም የተረባረበበት መሆኑን አውስተው፤ ግንባታው ሙሉ በመሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ  አስተዋጽኦቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ሁሉም ወገን   ለግድቡ ግንባታ ስኬት መተባበር እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።

የሐረሪ ክልል ል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊና በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ እንዳስታወቁት፤ ዘንድሮ በክልሉ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ሽያጭ  ተሰብስቧል።


 

ከገቢ አሰባሰብ ስራ በተጨማሪ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ  እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 

በሐረሪ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ሲደረግ የቆየውን ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉም ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም