ቀጥታ፡

አዲሱ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ደንብ የኢትዮጵያ የካርበን ሽያጭ በህግ እንዲመራ የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2016(ኢዜአ)፦ አዲሱ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ደንብ የኢትዮጵያ የካርበን ሽያጭ በህግ እንዲመራ የሚያደርግና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች  ገለጹ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሳባው ላይ ተወያይቶ እንዲጸድቅ ውሳኔ ካሳለፈባቸው የህግ ማዕቀፎች መካከል አንዱ "የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ" ነው።

ደንቡም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት የካርቦን ክምችትን በዓለም አቀፉ ግብይት በማስገባት የኢትዮጵያን የደን ሃብት ለማልማትና ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።  

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ከፍተኛ የደን ባለሙያዎች፤ የኢትዮጵያ የደን ሃብት በሚገባ በማልማት የካርቦን ሽያጭ ገቢዋን በማሳደግ ረገድ አዲሱ ረቂቅ ደንብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የብሔራዊ ‘’ሬድ ፕላስ’’ ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የካርበን ሽያጭ ማከናወን የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እስካሁን እንዳልነበራት ገልጸዋል።

በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሳባው ያጸደቀው የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ደንብ የደን ልማት፣ አጠቃቀምና የካርበን ሽያጭ የህጋዊነት ጥያቄን ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የደን ሃብቷን በማልማት ከዘርፉ የሚገባትን ገቢ እንድታገኝና በህጋዊነት ላይ የነበረውን የአሰራር ክፍተት ምላሽ የሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል። 


 

የኢትዮጵያ ደን ልማት ከፍተኛ የደን ባለሙያና የአገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፤ በደን ልማት ላይ የመጣውን ተጨባጭ ውጤት በደንብና ህጋዊ የአሰራር ሥርዓት መምራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘርፉን ልማት በማሳለጥ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳለጥ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ አዲሱ ደንብ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ መተላለፉ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም