ወጣቱ ትውልድ የአድዋን ታሪክ መነሻ በማድረግ አገሪቱን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያሻግር የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት - ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ የአድዋን ታሪክ መነሻ በማድረግ አገሪቱን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያሻግር የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት - ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ወጣቱ ትውልድ የአድዋን ታሪክ መነሻ በማድረግ አገሪቱን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያሻግር የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት ስትል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተናገረች።
በዓለም አደባባይ የአገሯን ሰንደቅ ያውለበለበችው የኦሊምፒክ ባለድሏ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የአድዋ ድል በከባድ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው ብላለች።
በአድዋ የተገኘው ድል ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ጠቁማ እያንዳንዱ ትውልድ የአገሪቱን ሥም በበጎ የሚያስጠራበት የራሱ ታሪክ የሚጽፍበት አድዋ ሊኖረው እንደሚገባም ተናግራለች።
ለዚህም ደግሞ ማንኛውም ግለሰብ በየዘመኑና በተሰማራበት ሙያ የሚጠበቅበትን አገራዊ ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲችል መሆኑን ገልጻ ይህም የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ነው ብላለች።
ጎን ለጎንም ትውልዱ የቀደሙ አባቶችን የአንድነትና አብሮነት እሴቶች ለማጠናከር ከአድዋ ጀግኖች ጽናትና አገር ወዳድነት እሴት በመውረስ ለአገር ከፍታ በትኩረት መሥራት እንዳለበትም ነው ያሳሰበችው።
የአድዋ ድል በትውልዶች ሁሉ ሊዘከር የሚገባው ደማቅ የጋራ ታሪክ መሆኑን ያነሳችው ደራርቱ፣ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር የተሻለ አገር ለመገንባት መሥራት እንደሚገባቸው ተናግራለች።
በተለይም በዚህ ዘመን የአገር ሰላም በማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርባለች።