የወላይታ ሶዶ ከተማ ኤሌክትሪክ ሀይል ማሰራጫ ጣቢያ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ሶዶ ከተማ ኤሌክትሪክ ሀይል ማሰራጫ ጣቢያ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ሶዶ ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ ባጋጠመው የእሳት አደጋ አገልግሎቱ የተቋረጠው የወላይታ ሶዶ ከተማ ኤሌክትሪክ ሀይል ማሰራጫ ጣቢያ ጥገና ተደርጎለት ወደ ስራ መግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት ዲስትሪቡዩሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገረሱ ቴጋ ከትናንት በስቲያ ምሽት 5:00 ላይ በጣቢያው ድንገተኛ የእሳት አደጋ መከሰቱን አስታውሰዋል።
በአደጋውም በጣቢያው የሚሰጠው አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር የገለጹት አቶ ገረሱ፣ "ከማሰራጫ ጣቢያው ሀይል በሙሉና በከፊል የሚያገኙ የወላይታ፣ ሃላባ፣ ጌዴኦ፣ ጋሞ፣ ካምባታ እና ሀዲያ ዞኖች የሀይል መቋረጥ አጋጥሟቸው ነበር" ብለዋል።
የደንበኞችን ጥያቄ ለመመለስ በተደረገ አፋጣኝ የጥገና ሥራም ጣቢያው በዛሬው እለት ሙሉ ለሙሉ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በዚህም የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ ሁሉም አካባቢዎች ዳግም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በነዚህ አካባቢዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የመልሶ ግንባታና አቅም ማሳደጊያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አያይዘው ገልጸዋል።