ቀጥታ፡

አባቶቻችን በአድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል

ጋምቤላ/ሰመራ/ሆሳዕና/ድሬዳዋ ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ አባቶቻችን በአድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ትውልዱ ኃላፊነቱን  መወጣት እንዳለበት የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

128ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በጋምቤላ፣ በሰመራ፣ በሆሳዕናና በድሬዳዋ ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። 

በጋምቤላ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዌይ ጆክ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጀግንነት፣ የአንድነትና የነፃነት ተጋድሎ ብሔራዊ ዓርማ ነው ብለዋል። 


 

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት በተባበረ ክንዳቸውና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸው ወራሪ ኃይልን በማንበርከክ የሀገራቸውን ክብር ከፍ አድርገው ለዓለም ጥቁር ህዝቦች አሸናፊነትን ያሳዩበት ድል መሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በዘመኑ ተንሰራፍቶ የነበረውን አፍሪካን የመቀራመት አጀንዳ በሃይል መስበር እንደሚቻል ያሳዩበት አንፀባራቂ የድል ታሪክ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድ በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር በአድዋ ድል የታየውን የህዝብ አንድነትና የሃገር ፍቅር በመጠበቅ የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል።

የክልሉ ባሀልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ፣ የአድዋ ድል አባቶቻችን በአንድነት ቆመው፣ አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ሀገርን ያፀኑበት የድል ቀን እንደሆነ ገልጸዋል። 


 

በአድዋ ጦርነት ወቅት መስዋትነት ለከፈሉ ጀግኖች አባቶቻችን  ክብራቸውን ለመዘከር የሚያስችል የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም  በአዲስ አበባ ተገንብቶ ለህዝብ እይታ ክፍት በሆነበት ማግስት  መከበሩ  የዘንድሮው የድል በዓል ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ አኩዋይ አቡቲ በሰጡት አስተያየት አድዋ የኢትዮጵያ ህዝቦች ታላቅ ታሪካዊ ድል መሆኑን ጠቅሰው የዘመኑ ትውልድ በሰላም በልማትና በኋላ ቀር አስተሳሰቦች ላይ በመዝመት የአባቶቹን ታሪክ ሊደግም ይገባል ብለዋል፡፡

የአድዋ ድል 128ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የተከበረ ሲሆን፣ በዚሁ ጊዜ የአፋር ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢሴ አደን፣ አድዋ ከመላው የአገሪቱ የዘመቱ አባቶቻችን የጋራ ጠላትን አንድ ሆነው ማሸነፍ እንደሚቻል ለዓለም ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።

የአፋር ክልል ሕዝብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እንደማይደራደር አመልክተው፣በጋራና ለጋራ የሆነችውን አገርን በጋራ ኃላፊነት መገንባት ይገባልም  ብለዋል።

በአድዋ አርበኞች የድል መንፈስ በዚህ ዘመንም በተለያዩ ሁነቶች መታየቱን ያስታወሱት አቶ ኢሴ፣ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የታየው ተነሳሽነትና ርብርብን መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ተወካይ ኮሎኔል ሙስጠፋ ዩሱፍ፣ ኢትዮጵያ ትውልዶች በከፈሉት መስዋዕትነት ጸንታ መቆየቷን አውስተዋል።


 

የአድዋን ድልን የሚዘክር ሙዚዬም በአዲስ አበባ መገንባቱ ትውልዶች የአባቶቻቸውን አኩሪ የነጻነት ተጋድሎና ታሪክ ለማወቅ እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

 የአሁኑ ትውልድ የአድዋን ታሪክ በኃላፊነትና በቅብብሎሽ ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ በኃላፊነት ሊወጣ ይገባዋልም ብለዋል።

በዓሉ ላይ የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል፣ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ አባላት፣ የፌዴራልና የአፋር ክልል ፖሊስና የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ በሆሳዕና ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳሉት፣ አድዋ በዜጎች የተባበረ ክንድና መስዋዕትነት የተገኘ አኩሪ ድል በመሆኑ ሁሌም ሊዘከር ይገባዋል።


 

የአድዋ ድል የመላው የጥቁር ህዝቦች ድል በመሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ በተምሳሌትነት እንድትጠቀስ አስችሏል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጎን በመሰለፍ ለድሉ መገኘት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አቶ አንተነህ ገልጸዋል።

በድሬዳዋ በተከበረው 128ኛ የአድዋ በዓል ላይ የታደሙ  ነዋሪዎችም አባቶቻችን በጠንካራ አንድነት አድዋ ላይ ከሰሩት ታላቅና ድንቅ የነፃነት ድል በመማር በተባበረ አንድነት ከድህነት ለመውጣትና የተሻለች አገር ለትውልድ ለማስረከብ የተጀመረውን ሥራ ለማሳካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በፓናል ውይይት በተከበረው በዓል ላይ የታደሙ  ነዋሪዎች የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችን በተባባረ ክንድ የኢትዮጵያን ነፃነት አስከብረው ነፃነቷ የተረጋገጠ አገር ያስረከቡበት ታሪካዊ ቀን መሆኑንም አንስተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም