ቀጥታ፡

የአድዋ ድል የሕዝብ አንድነትና ኅብረት የተንፀባረቀበት ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ነው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016 (ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የሕዝብ አንድነትና ኅብረት የተንፀባረቀበት ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ መሆኑን በመታሰቢያ በዓሉ የተገኙ የተለያዩ አገራት ተወካዮች ገለጹ። 

በ128ኛ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች የአድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ድል መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የአርመንያ አምባሳደር ሳሃክ ሳርግስያን፤ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለጥቁር ሕዝቦች ወሳኝ የድል ታሪክ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአድዋ ድል ጥንካሬ፣ ትብብር፣ የአገር ፍቅር፣ መስዋዕትነት የተንፀባረቀበት ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ መሆኑን ገልፀዋል። 

በመሆኑም 128ኛ የአድዋ ድል መታሰቢያ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ክብር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኤምባሲ የፖለቲካና አስተዳደር አማካሪ ናዋ ሲቦንጆ፤ የአድዋ ድል ለአፍሪካ አህጉር ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው ለሀገር ሉዓላዊነት በሕብረት የተሳተፉበት በመሆኑ የአንድነት ምሳሌ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከአድዋ ድል አፍሪካውያን ልዩነታቸውን በመቻቻል የበለፀገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር ትምህርት የምንወስድበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ ኤምባሲ የመከላከያ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ጂኤም ሻሪፉል፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለቅኝ ግዛት ባለመንበርከክ ኃያልነታቸውን ያሳዩበት ወሳኝ የድል ታሪክ መሆኑን ገልፀዋል።

ድሉም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያውያን በአንድነት የፋሽስትን ወራሪ ኃይል ድል ያደረጉበት 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም