የአድዋ ድል እሴቶችን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል እሴቶችን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ
አርባ ምንጭና ደብረ ብርሃን ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል መልካም እሴቶችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም መስፈን መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ።
የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ የአብሮነት ታሪክ በመማር አስተሳሳሪ የጋራ ትርክትን ማጠናከርና ኢትዮጵያን ማጽናት እንዳለበት ተመላክቷል።
128ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአርባ ምንጭ እና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በዓሉ በአርባ ምንጭ ከተማ "ዝክረ አድዋ ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ነው በድምቀት የተከበረው ።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ እንዳሉት፣ የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ የጋራ ታሪክ በመማር አስተሳሳሪ የጋራ ትርክትን ማጠናከርና ኢትዮጵያን ማጽናት ይኖርበታል።
ጀግኖች አባቶች ከየአቅጣጫው በመምጣት ለአገር ክብር በአንድነት በመዋደቃቸው በጠላት ላይ ድል ከመቀዳጀት ባለፈ የአገርን ሉአላዊነት ጠብቀው ማቆየት ችለዋል ብለዋል።
"የአሁኑ ትውልድም ከአድዋ የአብሮነትና የአሸናፊነት ታሪክ በመማር ልዩነትን ከሚያሰፉ ይልቅ ብሔራዊና ገዢ ትርክት ማጠንከር ይኖርበታል" ብለዋል፡፡
ለእዚህም የአድዋ ድል መልካም እሴቶች ለትውልዱ በማስረጽ በኩል የትምህርት ተቋማት በምርምር የተደገፈ ስራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሚስተዋሉ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በውይይትና በምክክር በመፍታትና የሥራ ባህልን በማጠንከር የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥና አዲስ ታሪክ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱርዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ዱባለ በበኩላቸው "የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የጥንት አባቶች የአገርን ክብር ያስጠበቁበትን ታሪክ የአሰባሳቢ ትርክት መገለጫችን ነው" ብለዋል።
አድዋ ድል ኢትዮጵያ በመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል ሆና እንድትታይ ማድረጉን አስታውሰው፣ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት ያሳዩትን ህብረት ለጠንካራ ሀገረ መንግስትና ለሰላም እሴት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
"የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት ነው" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ናቸው።
አድዋ የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የጽናት ውጤት በመሆኑ የዛሬው ትውልድ የአድዋን የእንድነት እሴቶች ለአገር ከፍ ያለ ስራ በመስራት ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ ከአባቶች ልቆ እንጂ አንሶ መገኘት እንደሌለበት ጠቁመው፣ "የሀገር ሰላምና ልማትን በዘላቂነት የማረጋገጥ ሃላፊነት አለብን" ብለዋል፡፡
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን በመድረኩም ምሁራን፣ የጋሞ እና ጎፋ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ ዜና የ128ኛ የዓደዋ ድል በዓል “አድዋ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር የሺሀረግ ጌታነህ በበዓሉ ላይ እንዳሉት፤ የዓደዋ ድል በኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ በአገራዊ ፍቅርና አርበኝነት ተጋድሎ የተገኘ የጥቁር ህዝቦች ድል ነው።
የዓድዋ ድል መልካም እሴቶችን በጥናትና ምርምር ደግፎ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም መስፈን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው በታሪክ የትምህርት ክፍሉ ወጣቱ ትውልድ ስለዓድዋ ድል በጥናት ላይ የተመሰረተ እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጥ የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጥዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ባምላክ ጌትነት በበኩሏ ፤የጥንት አባቶች በአንድነትና በጽናት ታግለው ለቅኝ ግዛት የመጣን ተስፋፊ ሀይል አሳፍረው መልሰዋል ብላለች።
የዛሬው ትውልድም በአድዋ መንፈስና እሴት ጥላ ስር ሆኖ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ አገርን ከፍ የሚያደርግ ስኬት ማስመዝገብ እንዳለበት ተናግራለች።
''ከአድዋ ድልን ብቻ ሳይሆን መተባበርን፣ አንድነትን፣ መቻቻልና ፍቅርን ጭምር ነው የተማርነው '' ያለው ደግሞ በዩኒቨርስቲው ኢንፎርሜሽን ሲስተም የ3ኛ ዓመት ተማሪ ሳሙኤል ሞገስ ነው።
በመሆኑም ዛሬ እየተስተዋለ ያለውን “የእኔነት አስተሳሰብ“ አስወግደን በእኛነት ስሜት ለአገር እድገት ጠንክረን መስራት አለብን ብሏል።
በዩኒቨርሲቲዎቹ በ128ኛው የአድዋ በዓል ሲከበር የአድዋን ድል የሚዘክሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በክብረ በአሉ የየኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና መምህራን የተገኙ ሲሆን አድዋን የሚዘክሩ ፁሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
---