128ኛው የአድዋ ድል በዓል በኳታር እና በቴል አቪቭ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
128ኛው የአድዋ ድል በዓል በኳታር እና በቴል አቪቭ ተከበረ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦128ኛው የአድዋ ድል በዓል በቴል አቪቭ እና በኳታር በተለያዩ መርሀ-ግብሮች ተከበሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኳታር ለበዓሉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት የቀደምት አባቶቻችንን በአንድነት ላይ የተመሠረተ አኩሪ የድል ታሪክ በመጠቀም እና በወንድማማችነት መንፈስ ወቅቱ የሚጠይቀውን የአርበኝነት ተግባር እንፈጽማለን ብለዋል።
በሀገር ልማት ላይ በንቃት በመሳተፍና ኋላ ቀርነትን ታሪክ በማድረግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በሀገራችን እውን ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የአርበኝነት መገለጫ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ኢንቨስትመንት በማድረግ በሀገር ግንባታ እና ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይም በቴል አቪቭ በተከናወነው የ128ኛው የአድዋ የድል በዓል አከባበር ላይ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ እንዳሉት የአድዋ ድል ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ ነው።
የኤምባሲው ሰራተኞች ፣ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች እንግዶች በታደሙበት በዓል ላይ አምባሳደሩ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ አኩሪ ታሪክ ለሌሎች ድሎች መነሳሳትን የሚያወርስ ነው ሲሉም መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።