መንግስት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መርሆዎችን መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መርሆዎችን መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መርሆዎችን መተግበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
6ኛው የኢትዮጵያውያን ቀን “ህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያ በቀጠር” በሚል መሪ ሀሳብ በኳታር ዶሃ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል።
ዝግጅቱን በኳታር-ዶሃ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማኀበር ዶሃ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር መዘጋጀቱም ተገልጿል።
የበዓሉ የክብር እንግዳ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም መንግስት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው ጋር የሚያስተሳስሩ ድልድዮችን የሚገነቡ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ የዜጎች መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መርሆዎችን መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በዓሉ በሀገራችን ለ128ኛ ጊዜ በሚከበረው የአድዋ ድል በዓል ወቅት የሚከበር መሆኑ ከሌሎቹ በዓላት ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በዓሉ በዚህ ዕለት መከበሩ ቀደምት አባቶቻችን ለሀገራቸው ነጻነት በአንድነት በመቆም መራር ተጋድሎ ያደረጉበትና የሀገራችንን አንድነት አስጠብቀው የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት ማድረግ የቻሉበት ቀን የምናስብበት ታላቅ ቀን እንደሆነም ገልፀዋል።
በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህን መሰል በዓላትን በማዘጋጀት በተለያዩ ኩነቶች የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለሌሎች በማቅረብ ሀገራቸዉን በማስተዋወቅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ለሀገራቸዉ አምባሳደር ሆነዉ እየሰሩ በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም መንግስት በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከየሀገሩ ጋር የሚያስተሳስሩ ድልድዮችን የሚገነቡ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን፣ የዜጎች መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መርሆዎችን መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በኳታር ኢ.ፌ.ዴ ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ በበኩላቸው በየዓመቱ የሚከበረው ይህ በዓል ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በመሰባሰብ የሀገር ገጽታ እንዲገነቡ የሚደረግበት በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዜጎቻችን እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን በአንድ ጥላ በማሰባሰብ በክፉም በደጉም አብረው እንዲቆሙ፣ ወንድማማችነታቸውንና እህትማማችነታቸውን እንዲያጠናክሩ ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ አሚኑ ኑሩ ማህበሩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ መብታቸዉንና ጥቅማቸዉን ስለሚከበርበት ሁኔታ እንዲወያዩ እንዲደጋገፉ ስለ ሀገራቸዉ ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ማንነታቸዉን የሚገልፁ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻቸዉን በማክበር እና ለሌሎች እንዲያስተዋዉቁ ማድረግ እንዲሁም በሀገራቸዉ በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ማድረግ መሆኑንም በማከል።
በበዓሉ የተለያዩ የጥበብ ስራዎች መቅረባቸውንና የእግር ኳስ የፍፃሜ ውድድር፣ እንዲሁም በርካታ አዝናኝ ፕሮግራሞች መከናወናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።