ቀጥታ፡

በ2016 "የኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ የአገር ውስጥ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ለማስፋት በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦  በ2016 "የኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ የአገር ውስጥ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ። 

"ኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ 2016 የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል። 


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ፤ የኤክስፖው ዓላማ በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችን በማስተዋወቅ የገበያ ድርሻቸውን ማሳደግ ነው ብለዋል። 

የውጪ ቴክኖሎጂዎችንና ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንዲሁም በአምራቾች መካከል ትብብርን መፍጠር ሌላኛው የኤክስፖው ዓላማ መሆኑንም ነው ያስረዱት።   

በተለይም የአገር ውስጥ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ለማስፋት ኤክስፖው በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።   

መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾችን የገበያ ድርሻ ለማስፋት የኢትዮጵያን "የተኪ ምርት" ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አመላክተዋል። 

የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ለማሳደግ የመንግሥት ተቋማት ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲገዙ አቅጣጫ መቀመጡንም እንዲሁ። 

ከዚህ በፊት የተካሄዱ "የኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖዎች የታለመላቸው ግብ ማሳካታቸውን ተገልጿል። 

በተለይም አልባሳትን፣ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን በሥፋት በማምረት ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡንም እንዲሁ።  

በመርኃ ግብሩ የተገኙት አምራቾች መሰል ኤክስፖዎች ከሌሎች አምራቾች ጋር በትብብር እንድንሰራ እስችሎናል ብለዋል። 

በዚህም ከግል ተጠቃሚነት ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።  

ኢትዮጵያ ታምራት ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

የ2015 "ኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ ከ450 በላይ ተጋባዥ እንግዶች የተገኙበት፣ ከ50 ሺህ በላይ ጎብኝዎች የታደሙበት፣ 125 የንግድ ሥምምነቶች የተፈረሙበትና ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት የተፈጸመበት እንደነበር ተጠቁሟል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም