ሞክሼዎቹ - የአድዋ መንገሻዎች

3765

                              ሞክሼዎቹ - የአድዋ መንገሻዎች

                             (ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም እና ራስ መንገሻ ዮሐንስ)

 

የአድዋ አድማስ ዘለል ገድል ሲወሳ የድሉ መገኘት የጦር አበጋዞች ከፊት ይመጣሉ። ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ ራስ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች፣ ግራዝማች፣ ባላምባራስ እና ሌሎች ባለማዕረግ አዋጊዎች የድሉ የጀርባ አጥንት መሆናቸው እሙን ነው። ከመላ ሀገሪቷ ጠረፍ ተነቃንቆ ስንቅና ትጥቁን ታጥቆ፣ ድል ሰንቆ እስከ ግማሽ ዓመት ድረስ በባዶ እግሩ የተመመውን የሀገሬው ሰራዊት በቅጡ መርተው አዋግተዋል። 

ከመነሻ ሰፈር እስከ አድዋ ተረተር፣ ከአምባላጌ ኮረብቶች እስከ መቀሌ ጋራና ቁልቁለቶች፣ ከእንደአባ ገሪማ እስከ ማሪያም ሸዊቶ ሸለቋማ ቋጥኞች፣ ከምንድብድብ መስክ እስከ በገሠሦ አቆበቶች፣ .... ድልና ገድል በደምና በላብ ሲጻፍ  የጠላትን የ'ክዱ' ማባባያ የጠሉ፣ ለሀገር ለመሰዋት የቆረጡ ጀግና አዋጊዎች፣ የሀገር ባለውለታዎች ነበሩ። 

በአድዋ ድል መታሰቢያ 12 የአድዋ ጦር አበጋዞች (ጀኔራሎች) ሀውልት ቆሞላቸዋል። እነሱም፤- ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ ጉርሙ (አባ ጎራው)፣ ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ (አባ ቃኘው)፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት ተሰማ ጎሹ (አባ ጠና)፣ ንጉስ ሚካኤል አሊ አባ ቡላ (አባ ሻንቆ)፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮቢ (አባ ጠለስ)፣ ራስ ቢተወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፉ (አባ ገድብ)፣ ራስ ወሌ ብጡል ሃይለማሪያም (አባ ጠጣው)፣ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ገብረመድህን (አባ መርከብ)፣ ራስ አባተ ቧያለው ንጉሱ (አባ ይትረፍ)፣ ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ (አባ ነጋ)፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ (ቁሴ) ዲነግዴ ሁንዱል (አባ መቻል) እና ራስ መንገሻ ዮሃንስ ምርጫ (አባ ግጠም) ናቸው።

ከነዚህ የአገር ባለውለታዎች መካከል ሁለት ስመ ሞክሼ ጀግኖችን እንዘክራለን። ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም እና ራስ መንገሻ ዮሐንስን።

ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቀዳሚዎች ስምንት ራሶች መካከል ብቸኛው የራስ ቢትወደድ (ከንጉሥነት በታች) ባለማዕረግ ናቸው። በፈረስ ስማቸው አባ-ገድብ ይሰኛሉ። በልጅነታቸው የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ባለሟል ሳሉ ከእስረኛው ምኒልክ ጋር ተዋወቁ። ምኒልክ ከአፄ ቴዎድሮስ አምልጠው ሸዋ ከገቡ በኋላ ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ወንድሞች ራስ ወሌ እና ፊታውራሪ አሉላ ብጡልን ይዘው ከመቅደላ ወደ ሸዋ ተሻገሩ፤ የምኒልክ ሁነኛ ሰው ሆኑ። 

ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም በሞት እስኪለዩ ድረስ በክፉም በደጉም ዘመን የአጼ ምኒልክ ከፍተኛ አማካሪና ተወዳጅ መስፍን እንደነበሩ፣ ከጦር ሜዳ እስከ ሽምግልናም ሁነኛ ሰው ሆነው ስለማገልገላችው በታሪክ ድርሳናት ተጠቅሷል። በሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ዳሞት(ጎጃም) ተዘዋውረው በተለያዩ ግዛቶች በአስተዳዳሪነት ሰርተዋል። ድሕረ መተማ ጦርነት ምርኮኞች እንዲመለሱ፣ ድንበር እንዲካለል በመስራትም የዲፕሎማሲ ስራቸው ይጠቅሳል። ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ከተሳተፉባቸው ደማቅ ታሪኮች መካከል የአድዋ ድል ይጠቅሳል።

ጦርነቱ አሀዱ ብሎ የጀመረው ሕዳር 28 ቀን 1888 አምባላጌ ነው። ለሁለት ሰዓታት በዘለቀው በዚህ ጦርነት ጀኔራል ቶዚሊ የተባለው የጠላት ጦር መሪ የተገደለበት ነው። በዚህ ዐውደ ውጊያ አባ ገድብ አንዱ ወሳኝ የጦር አበጋዝ ነበሩ። በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደተመዘገበው ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ከግዛታቸው ከዳሞትና አገው ምድር የተውጣጣ ስድስት ሺህ እግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር ይዘው አድዋ ዘምተዋል።

“አባ ገደብ መንጌ እያለ ኧረ ጐራው 


አምባ ላጌን ሰብሮ ቶዘሊን አስጐራው” የተባለው ለዚህ ይመስላል። 

አባ ገድብ ጥቅምት 11 ቀን 1903 ምሸት ከራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ጋር እየተጫወቱ ካለምንም ህመም ድንገት አርፈው ቅድስት ሥላሴ ተቀበሩ። 

ራስ ቢትወደድ መንገሻ ልጆቻቸውን ከተለያዩ መኳንንት ጋር በጋብቻ በማጣመር በኢትዮጰያ ታሪክ ተጠቃሽ መሆን ችለዋል። ለአብነትም ዘውዲቱ መንገሻ ጠቅላይ ሚኒስትር መኮንን እንዳልካቸውን፣ አስካለማርያም መንገሻ ልዑል ራስ ኅይሉን አግብተው የልጅ ኢያሱን ባለቤት ሠብለወንጌል ኅይሉን ወልደዋል። ደጃዝማች ጀኔራል አበበ ዳምጠውን ያገቡት ወሰንየለሽ መንገሻ ደግሞ የአልጋወራሽ አስፋወሰን ባለቤት ልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅ አበበን ወልደዋል።

ሌላው የአድዋ ጀግና የጦር መሪ ራስ መንገሻ ዮሐንስ (አባ ግጠም) ናችው። ትውልዳቸው ትግራይ፣ ዘመኑም 1857 ዓ.ም ነው። የአድዋ ጦር ውሎ ቁልፍ ሰው ራስ መንገሻ የአጼ ዮሐንስ (አባ በዝብዝ) ልጅ ናቸው። አጼ ዮሐንስ በተሰዉበት በመተማው ጦርነት ተሳትፈዋል። አባታቸው ከሞቱ በኋላም የትግራይ አገረ ገዥ ሆነዋል። 

በአድዋ ዘመቻ 12 ሺህ ጦር አሰልፈው በብርቱ ተዋግተዋል። ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ በአጼ ምኒልክ ላይ እንዲያምጹ ኢጣሊያኖች ሲገፋፋቸውና ሲያባብላቸው ቢቆዩም ከስልጣን ሽኩቻ ይልቅ የኢትዮጵያን ነጻነት መርጠዋል። ከአጼ ምኒልክ ጋር ቢኳረፉም በሀገር ሉዓላዊነት ግን አልተደራደሩም። የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ትግራይ ሲገባም ራስ መንገሻ የወገን ደጀን ጦር እስኪደርስ ወደራያ አፈግፍገው፣ በአምባላጌ ጦር ሜዳ አንዱ ተሳታፊ የጦር ጀግና ነበሩ።

ራስ መንገሻ የትግራይ ሀገረ ገዥ በመሆናቸውም የእርሳቸው እና በስራቸው የነበሩት የራስ አሉላ እንግዳ ጦር በጄኔራል አልቤርቶኔ ከሚመራው ጠላት ሃይል ቀዳሚው ተፋላሚ እንዲሆኑ አድርጎታል።

“አይከፈት በሩ መግቢያ መውጫችን

በል ተነስ መንገሻ ግጠም በር በሩን

ይህን ጎሽ ጠላ ማን አይቀምሰው

መንገሻ ዮሐነስ አንተን ገፍተው...” ተብሎ የተገጠመላቸውም ለዚህ ነው። የጠላት መግቢያ በር ዘብ በመሆናቸው።

አባ ግጠም በአድዋው ታሪካዊ ጦርነት አሰላለፋቸው ማርያም ሸዊቶ በተሰኘው ተራራ በኩል ሲሆን ከራስ አሉላ፣ ከዋግሹም ጓንጉል ብሩና ከደጃዝማች ሀጎስ ጋር በመሆን ነበር። የጠላትን የመጀመሪያ ጥቃትን ያስተናገዱትም ራስ መንገሻ ዮሐንስ ናቸው። የአድዋ ድል ከተበሰረ በኋላ አጼ ምኒልክ ራስ መንገሻን ሹመውና ሸልመው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። አጼ ምኒልክ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ማህበረሰቡ በጦርነት ስፍራ በመሆኑ ለደረሰበት ጉዳት 30 ሺህ ብር ድጋፍ ማድራገቸውን የንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕል የጻፉት ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደአረጋይ ተርከዋል። 

ከአድዋ ድል ከጥቂት ዓመታት በኋላ ራስ መንገሻ በአጼ ምኒልክ ላይ በማመጻቸው ተይዘው በቁጥጥር ስር ዋሉ። ሕዳር 6 ቀን 1899 ዓ.ም አንኮበር ግዞት ላይ አንዳሉ ማረፋቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከራስ መንገሻ አቲከም ግዛት ከአገው ምድር እመይቴ ተዋበች ጋር ትዳር መስርተው ዕውቁን የትግራይ መስፍን ራስ ሥዩም መንገሻን እንዲሁም ከእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ወይዘሮ ከፈይ ወሌ ብጡል አግብተው አስቴር መንገሻን፣ አልማዝ መንገሻንና ብርሃኔ መንገሻን ወልደዋል፡፡ 

ለአብነት ያክል የሞክሼዎቹን ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም እና ራስ መንገሻ ዮሐንስ አነሳን እንጂ የዛሬ የ128 ዓመት በአድዋ ጦርነት ዓለም የተደመመበትና ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ የሆነበት ደማቅ ታሪክ የጻፉ ጀግኖች ቁጥር ስፍር የላቸውም።

ጀግኖቹን የመሩ የጦር መሪዎችም ብዙና ተጋድሏቸው የገዘፈ ነው። ከ11 ሺህ በላይ የጣሊያንን ሠራዊት  ሙትና ቁስለኛ ያደረጉ፣ 4ሺህ የሚሆኑትን እጅ ያሰጡና የማረኩ እንዲሁም 56 መድፎች፣ በርካታ መትረየሶች እና ሌሎች አውቶማቲክ መሳሪያዎቹን ለወገን ጦር እንዲያስረክብ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሁል ጊዜም ክብር ይገባቸዋል። 

የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር አድርጎ ለመበዝበዝ ቢመጣም ጀግንነት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ እንዲሁም የአልገዛም ባይነት ወኔን የታጠቁ ኢትዮጵያውያን በሶሎዳ ተራሮች ግርጌ ቅስሙን በመስበር የአገራቸውን ክብርና ነጻነት አጽንተዋል።

በዚህ አኩሪ ድል ኢትዮጵያ ለበርካታ አገራት በተምሳሌትነት ትጠቀሳለች። የአድዋ ድል ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህዝቦች የጀግንነት ተምሳሌትና የነጻነት ዓርማ እንድትሆን ያስቻለ ታላቅ አፍሪካዊ ድል ነው። 

(በአየለ ያረጋል)

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም