የአድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፣ የወል እውነትና አብሮነትን በጽኑ መሰረት ላይ ያኖረ ነው - አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፣ የወል እውነትና አብሮነትን በጽኑ መሰረት ላይ ያኖረ ነው - አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፣ የወል እውነትና አብሮነትን በጽኑ መሰረት ላይ ያኖረ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
128ኛው የአድዋ ድል በዓል በአድዋ መታሰቢያ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አድዋ የአብሮነት የድል ውጤት ነው።
በድሉ፤ ኅብረት ገኖ የታየበት፣ መሪና ተመሪ የተናበቡበት፤ ከእኔነት ይልቅ እኛነት ተዳምረውና ተናበው ኃይል የፈጠሩበት አውድ ነው ብለዋል።
አብሮነት መናበብና አንድነት ሲደመሩ ወኔን፣ ጥበብንና ጉልበትን ይፈጥራሉ፤ የሚፈለገው ግብ ጋር ለመድረስም ጉዞውን ያፋጥናሉ ሲሉ ተናግረዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የጀመርነውን ጉዞ ከግብ ለማድረስ አብሮነትና የጋራ ራዕይ ሊኖረን ይገባልም ነው ያሉት።
የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም አደባባይ ገኖ እንዲወጣ ያስቻለና ኢትዮጵያዊነትም የክብር መጠሪያ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በባርነት ለሚማቅቁ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ ስንቅና ትጥቅ ሆኖ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ወኔ የሰነቁበት ነው ብለዋል።
ድሉ ከሁሉም ድሎች ልቆ አሁንም ድረስ አንጸባራቂ ሆኖ የመቀጠሉ ምስጢር የአይቻልምን መንፈስ በመስበር በዓለም አደባባይ የመሰከረ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በአድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን የበላይነት ያደረ እውነት ተደርጎ በሚወሰድበት በዛ በጨለማ ዘመን አዲስ እውነትን ያዘለች ጸሃይ በሰንሰለታማ አድዋ ተራሮች አናት ላይ ወለል ብላ ወጥታለች ብለዋል።
የአድዋ ድል ጨለማን በብርሃን የገሰሰች፤ ሐሰትን ለእውነት ያስገበረች፤ የበላይነትን ክፉ እሳቤ ሰብራ እኩልነትን ያነበረች የአይበገሬነት ጸሃይ በአድዋ ድል ላይ ለመላው ዓለም ወጥታ የታየችበት ድል ነው።
የአድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፤ የወል እውነትና አብሮነትን በጽኑ መሰረት ላይ ያኖረ ነው ብለዋል።
የአድዋ ድል በተለምዶ አውነት የሚመስለውን የነጭ የበላይነት የሃሰት ትርክት በእውነተኛው የእኩልነት ትርክት የቀየረ የዓለም ጉልህ የታሪክ ክስተት መሆኑንም ተናግረዋል።
የዘንድሮ የአድዋ ድል በዓል ለየት የሚያደርገው ታሪኩን የሚመጥን በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ የመታሰቢያ ሃውልት በተገነባ ማግስት መሆኑ ነው ብለዋል።
መታሰቢያው የአድዋን ታሪክ በአግባቡ ለመሰነድና ቀጣዩ ትውልድ ከአባቶቹ ታሪክ ተምሮ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የራሱን ታሪክ ለመሥራት ያስችለዋል ነው ያሉት።
ለዚህ የአድዋ መታሰቢያ እውን መሆን በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን አመስግነዋል።