ትላንትን ከዛሬ ባስተሳሰረው የአድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኙ እውነታዎች 

2550

ትላንትን ከዛሬ ባስተሳሰረው የአድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኙ እውነታዎች 

ለመነሻ 

እኤአ በ1885 ጀርመን በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ አውሮፓውያን መላ አፍሪካን በካርታ ላይ የተከፋፈሉትን በተግባር መሬት ላይ ለመቀራመት ጦራቸውን ሰብቀው፣ ስንቃቸውን ጭነውና ትጥቃቸውን አጥብቀው ያካሄዱት ዘመቻና የወረራ ጉዞ የተገታባት አድዋ እና እለቷ ዛሬ ድረስ በተገፉ ህዝቦች ልብ ታትማ በአዕምሮ ውስጥ ተቀርጻ ትኖራለች። ጣሊያን የኢትዮጵያን መሬት፣ የአየር ንብረትና መልክዓ ምድር ተቆጣጥሮ ሀብቷን ለሮምና ለመላው አውሮፓ ለማቅረብ የቋመጠበት የዘመናት ህልሙ የተኮላሸበት ቦታ ጭምር ናት - አድዋ። 

ይህ ወራሪ ኃይል ሊቢያን በእጁ ካስገባ በኋላ ጉዞውን በቀይ ባሕር አስመራ አድርጎ መላ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ግብ ነበረው። ጄነራል ባራቴሪ የመደባቸው ጄነራል አልበርቶኒ፣ ጄኔራል አሪሞንዲ እና ጄነራል ቦርሜዳ በግንባር የተሰለፈውን ጦር ሲመሩ የኋላ ደጀንም እንደነበራቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከ17 ሺህ በላይ የጣሊያን ሠራዊት 66 የሚሆኑ መድፎች፣ በርካታ መትረየሶች እና አውቶማቲክ መሳሪያዎችን ታጥቆ የግንባር ሜዳው ላይ ስለመድረሱ "የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስካሁኑ ዘመን" በሚል በአንድርዜይ ባርይትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል-ኒየችኮ ተጽፎ በዓለማየሁ አበበ የተተረጎመው መጽሐፍ ያስረዳል። 

የዛሬ የ128 ዓመት፤ ዕለቱም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት ዓለም የተደመመበትና ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ የሆነበት ደማቅ ታሪክ በጀግኖች አባቶች ተሰራ። በጦርነቱ የጣሊያን መንግስት የጎመጀውን የኢትዮጵያን መሬት ሊያገኝ ይቅርና ከ11 ሺህ በላይ ሠራዊቱ ሙትና ቁስለኛ ሆኑ። 4ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ለጀግኖች አባቶቻችን እጃቸውን ሰጥተው ተማረኩ። እንዲሁም 56 መድፎች፣ በርካታ መትረየሶች እና ሌሎች አውቶማቲክ መሳሪያዎቹን ለወገን ጦር አስረከበ። 

 የቀረው የፋሽስት ሠራዊትም ተንጠባጥቦ እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈረጠጠ። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት በአውደ ግንባሩ በፈጸሙት የጀግንነት ተጋድሎ ዓለምን ያስደመመና መላውን ጥቁር ሕዝብ ያኮራ ድል ተጎናጽፈዋል። በወቅቱ ነጭን ታግሎ ማሸነፍ አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ በይቻላል ተክቶ ሌሎችም ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ ደማቅ የታሪክ አሻራ አኑረዋል። 

የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር አድርጎ ለመበዝበዝ ቢመጣም ጀግንነት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ እንዲሁም የአልገዛም ባይነት ወኔን የታጠቁ ኢትዮጵያውያን በሶሎዳ ተራሮች ግርጌ ቅስሙን በመስበር የአገራቸውን ክብርና ነጻነት አጽንተዋል።

በዚህ አኩሪ ድል ኢትዮጵያ ለበርካታ አገራት በተምሳሌትነት ትጠቀሳለች። የአድዋ ድል ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህዝቦች የጀግንነት ተምሳሌትና የነጻነት ዓርማ እንድትሆን ያስቻለ ታላቅ አፍሪካዊ ድል ነው።

ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢና በሌሎች ልዩነቶች ሳይነጣጠሉ ለአገራቸው ክብርና ነጻነት በአንድነት ቆመውና መስዋት ከፍለው ያስመዘገቡት የጀግንነት ታሪክ ነው።

በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለመላው የጥቁር ህዝቦች ኩራትና የነፃነት ምልክት ሆናለች፡፡ የሰው ልጆችን እኩልነት በደም ዋጋ አረጋግጣለች። 

 

የአድዋ ድል መታሰቢያ 

የአድዋ ድል ደማቅና ታላቅ ቢሆንም በሚመጥነው ልክ መታሰቢያ አልነበረውም። ዛሬ ግን እነዚያ ዋጋ የከፈሉ ጀግኖችን በሚመጥን ሁኔታ በአዲስ አበባ ፒያሳ “የዓድዋ ድል መታሰቢያ”  ተገንብቷል።

ከአድዋ ድል 128 ዓመታት በኋላ፣ የተሰራው የአድዋ ድል መታሰቢያ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ ተከፍቷል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ በአምስት ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን በአንድነት የተከፈለውን መስዋትነት፣ የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ፣ የሴቶችን ተጋድሎ በሚያሳይ መልኩ፣ በአስገራሚ የኪነ-ህንጻ ጥበብ የታነጸ ነው።

 

የአድዋ ድል መታሰቢያ የተገነባበት ስፍራ

አገር በውጭ ወራሪ ኃይሎች እጅ እንዳትወድቅ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የዓድዋ ጅግኖች የዘመቻቸው መነሻ እንዲሁም ከድል በኋላ ተሰባስበው ደስታቸውን የተጋሩበት ታሪካዊ ስፍራ ነው። 

የአድዋ ድል በዓል 7ኛ ዓመት ዳግማዊ ምኒልክ፣ ከአርበኞች፣ ከየአካባቢው ገዢዎች፣ ከውጭ አገር ዲፕሎማቶችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በደማቅ ሁኔታ በዚሁ ስፍራ አክብረውታል።

ስፍራው ዛሬ የታላቁ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሳይገነባበት በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ቢታጭም ውጤታማ ስራ ሳይሰራበት ቆይቷል። አካባቢው ለረጅም ዘመናት ታጥሮ ሳይለማ በመቆየቱ እጅግ የቆሸሸ፣ ሰዎች ለዝርፊያ የሚዳረጉበት ስፍራ ሆኖ ቆይቷል።

ዘመናትን ተሻግሮ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በከተማዋ ከሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በዓይነቱ ልዩ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሰራበት ተደረገ። 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ እጅግ በሚስብ ኪነ ህንፃ፤ የኢትዮጵያውያንን ህያው የድል ታሪክ የሚዘክር ሆኖ ተሰርቷል። 

 

የአድዋ ድል መታሰቢያ መግቢያ በሮች

የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት፣ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ኩራት የሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ መግቢያ በሮች የራሳቸው የሆነ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። የምሥራቅ ጀግኖች በር፣ የምዕራብ ጀግኖች በር፣ የሰሜን ጀግኖች በር፣ የደቡብ ጀግኖች በር፣ የፈረሰኞች በር፣ የአርበኞች በር፣ የፓን አፍሪካኒዝም በር ተብለው የተሰየሙ ናቸው። 

በአራቱም አቅጣጫዎች የተሰየሙ በሮች ተምሳሌትነት በዓድዋ ድል ከአራቱም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሳተፉበት የጋራ ድላቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ 

 

መታሰቢያው በውስጡ ምን ይዟል?

በዋናው መግቢያ:- የኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ነጻነት ድል መገለጫ የሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሃውልትና የሁሉም ከተሞች ርቀት ልኬት መነሻ የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ምልክት ይገኛል።

የዓድዋ ጦርነት ዘመቻን ያስተባበሩትና የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሀውልትም በዚሁ መግቢያ በኩል ይገኛል። 

ሃውልት የቆመላቸው 12 የጦር  መሪዎች:- በመታሰቢያው የአድዋን ጦርነት በታላቅ ጀግንነት በመምራት ለጥቁር ህዝቦች ድል ያበሰሩ 12 ዋና ዋና የጦር መሪዎች ሃውልት ተቀምጧል፣ እነሱም፤- ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ ጉርሙ (አባ ጎራው)፣ ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ (አባ ቃኘው)፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት ተሰማ ጎሹ ( አባ ጠና)፣ ንጉስ ሚካኤል አሊ አባ ቡላ (አባ ሻንቆ)፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮቢ (አባ ጠለስ)፣ ራስ ቢተወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፉ (አባ ገድብ)፣ ራስ ወሌ ብጡል ሃይለማሪያም (አባ ጠጣው)፣ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ገብረመድህን (አባ መርከብ)፣ ራስ አባተ ቧያለው ንጉሱ (አባ ይትረፍ)፣ ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ ( አባ ነጋ)፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ (ቁሴ) ዲነግዴ ሁንዱል (አባ መቻል) እና ራስ መንገሻ ዮሃንስ ምርጫ (አባ ግጠም) ናቸው።

በስተቀኝ በኩል፤- እስከ 3 ሺ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት የስብሰባ አዳራሽ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያው ኮሪደር ላይ ደግሞ ህዝቡ የጦርነት ክተት አዋጅ ጥሪ ሲሰማ ሁሉም ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው አገሩን ከወራሪ ለመታደግ በመወኔ መነሳቱን፣ ወደ ጦር ግንባር መትመሙን እንዲሁም በጀግንነት መፋለሙን የሚሳየዩ ትዕይንቶች  በእስክሪኖች ይታያሉ።

በክፍሉ መሐል ላይ፤- ጦርነቱ የተጎሰመበት ግዙፍ ነጋሪት የተቀመጠ ሲሆን በነጋሪቱ ግራና ቀኝ ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው የውጫሌው ውል አንቀጽ 17፣ የአድዋ ታሪክ እንዲሁም ከድል ወደ ሰላም የሚለው የአዲስ አበባ ስምምነት ሰነድ ተዘርግቶ ይገኛል።

ከድል መልስ ግልጋሎት ላይ የዋሉ ጋሻዎች፣ መሳሪያዎች፣ አልባሳት፣ መመገቢያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች፣ ስዕሎች፣ ፎቶዎች ይገኛሉ።

ወደ ውስጥ መግቢያ በሆነው በምዕራብ በር ላይ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አጼ ሚኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሃውልት በክብር ተቀምጦ ይገኛል።

በአድዋ ጦርነት ወቅት ጠላት ለመጠጥነት ይጠቀምበት የነበረውን የምንጭ ውሃ እቴጌ ጣይቱ ብልሃት በተሞላበት መልኩ በኢትዮጵያ ሰራዊት እንዲከበብና ጠላት በውሃ ጥም እንዲዳከም በማድረግ ማሸነፍ የተቻለበት የጦር እስትራቴጂ የሚዘክር ገንዳ ከእቴጌ ጣይቱ ሃውልት ፊት ለፊት ተቀምጦ ይገኛል። 

የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች፤- ጦርነቱ የተካሄደበትን ቦታ የሚያሳየው የአሸዋ ገበታ ሌላው የአድዋ ድል መታሰቢያ ውበትም ታሪክም ነው፡፡ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች፣ መልከዓ-ምድር የሚሳየው የመሬት ላይ ንድፍ ስራ በዚሁ መታሰቢያ መቀመጡ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለነጻነት የከፈሉትን መስዋትነት ያመላክታል። ከተራሮች አጠገብ በጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ ከዋሉ ጣሊያናዊ ስሪት የሆነ "ቶሪኖ 1883" የሚል ጽሁፍ ያለበት መድፍ ይገኛል።

በጦርነቱ ተዋጊዎችን ያጓጓዙ 45 ሺህ ፈረሰኞች የሰሩትን ጀብድ ሊወክልና ሊዘክራቸው የሚችል ‘የአድዋ ፈረሰኞች የድል ሀውልት’ ቆሞላቸዋል፡፡

የአድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያን ከወራሪው ጣሊያን ለማዳን ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት ተሰባስበው የተመሙበትን የሚወክል ‘የአንድነት ድልድይ’ በሚል ተሰርቷል፡፡ 

        

የሁሉንም ተሳትፎ የሚያሳዩ የተለያዩ ሁነቶች

በጦርነቱ ወቅት ህዝብና አገርን በታማኝነት ሲያስተዳድሩ የነበሩ እንደራሴዎች የሚያሳይ ስዕላዊ በመታሰቢያ የተቀመጠ ሲሆን በጦርነቱ ወቅት የነበረውን የህዝቡን እንቅስቃሴ የሚገልጹ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ ስዕሎችና ቅርጾችም ይገኛሉ።

 

   የገበሬዎችና ሴቶች ተሳትፎ የሚያሳዩ ስራዎች 

በአድዋ ጦርነት ከ120 ሺህ በላይ ገበሬዎች የግብርና ስራቸውን አቋርጠው "አገራችን ተነካች" በማለት ታጥቀው ድል ያጎናጸፉ፣ ለጥቁር ህዝቦች ትልቅ ታሪክ ያስቀመጡ ጀግኖች ናቸው። በዚህ መታሰቢያ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነጻነት ማስታወሻ የኢትዮጵያ ጀግኖችን ጉዞ የሚያሳዩ ምስሎች ይገኛሉ። 

በጦርነት ወቅት ሴቶች የቤት ሃላፊነትን ከመወጣት በተጨማሪ በአዋጊነት፣ በመረጃ ሰጪነት ቁስለኞችን በመንከባከብ ለሰሩት ስራ የተሰየመ ማስታወሻም በአድዋ ድል መታሰቢያ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። 

የአሁኑ ትውልድ አሻራ፣- የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት ተባብረው አፍሪካ በራሷ አቅም መልማት እንደምትችል ያሳዩበት፣ አፍሪካዊ ተምሳሌት የሆነው የህዳሴ ግድብ ፏፏቴ በመታሰቢያው ይገኛል። ኢትዮጵያውያን ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ላደረጉት ተጋድሎ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የፓን-አፍሪካ ሃውልትም ተካቷል። 

 

ሌሎችም 

የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ጦርነት ሁነቶች ብቻ ሳይሆን ለተለያያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ አዳራሾችን፣ ካፍቴሪያዎችን፣ ሲኒማ ቤቶችንና ሌሎች ለበርካታ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችንን አካቶ የተሰራ ነው። 

ከ2500 በላይ እንግዶችን መያዝ የሚችል ፓን አፍሪካን አዳራሽ፣ 300 ሰዎች የሚይዝ የአድዋ አዳራሽ፣ 160 ሰዎች የሚይዝ መካከለኛ አዳራሽ፣ 300 ሰው በአንድ የሚያስተናግዱ ሬስቶራንቶች፣ ሁለት ካፍቴሪያዎችና የህጻናት ሙዚየም በውስጡ አካቷል። 

በሌላ በኩል በአንድ ጊዜ 1000 ተሽከርካሪ መያዝ የሚችሉ ፓርኪንግ፣ ዘመናዊ ጂምና ሌሎችም ተካተዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ አድዋ ጊዜ የማይሽረው፣ ዘመን የማይለውጠው  የጀግንነትና የአንድነት ምልክት መሆኑን ማሳያ፣ ለነጻነት የታገሉና የተሰዉ ጀግኖች የሚታሰቡበት የታሪክ ማስታወሻ ነው።

የአድዋ ድል ትሩፋቶችን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብ በየትውልዱ ለማስተማር የሚያግዝ የዘመናት የነጻነት መንፈስን የሚያስተጋባ፣ ለመጪው ትውልድ የሚሻገር እውነት ነው።

እናም የአድዋ ድል መታሰቢያ የወል ታሪካችንን የምንገነባበት የማዕዘን ድንጋይ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም