ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት በሁሉም መስክ እየዘመነ ግዳጁን በብቃት በመወጣት እንደ አድዋ ጀግኖች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማስከበሩን ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአደረጃጀት፣ በትጥቅ፣ በስነልቦናና በአካላዊ ጥንካሬው እየዘመነ ግዳጁን በብቃት በመወጣት እንደ አድዋ ጀግኖች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማስከበሩን ይቀጥላል ሲሉ የጦር ኃይሎች  ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

128ኛው የአድዋ ድል በዓል የጥቁር ህዝቦች ድል በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የጦር ኃይሎች  ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ትጥቅ ተደራጅቶ ባህር ተሻግሮ የወረራትን የፋሺዝም ሃይል ድል ያደረገችው በህዝቦቿ አንድነት ነው ብለዋል። 

አድዋ ከኢትዮጵያ የድል አድራጊነት ታሪኮች ውስጥ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ትጥቅ ተደራጅቶ ባህር ተሻግሮ የወረራትን የፋሺዝም ሃይል የገጠመችው በፈተና ውስጥ ሆና ነበር ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፥ በወቅቱ ድርቅ በመከሰቱ ከብቶች ያለቁበትና ህዝቡም ለምግብ እጥረት የተዳረገበት ነበር ብለዋል።

ይሁንና በፈተና ውስጥ የሚፀናውና ሀገር በባዕዳን በተጠቃች ጊዜ አንድነቱ የሚጎለብተው፣ ቁጭቱና ወኔው ግለት የሚጨምረው እና የሀገር ፍቅር ስሜቱ  የሚጠነክረው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢ ልዩነቶች ሳይከፋፈል በአንድነት ወደ ውጊያ መዝመቱን ጠቅሰዋል።

በወኔ፣ በጀግንነትና በፅናት ተዋግቶ ወራሪን በማሸነፍ  አንፅባራቂ ድል ማስመዝገቡን ጠቅሰው፥  ድሉ አፍሪካን እንደ  ቅርጫ ተከፋፍለው የቅኝ ገዥ የበላይነታቸውን ዘላለማዊ የማድረግ ውጥን የነበራቸውን ሃይሎች  ክፉኛ ያስደነገጠ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ድሉ ትልቅነቱን የሚመጥን ዋጋ ሳይሰጠው በየዓመቱ ለትውስታ ብቻ እየተከበረ ቆይቶ፥ በዚህ ትውልድ ያማረ እና ታሪኩን በተሟላ ሁኔታ የሚዘክር የድል መታሰቢያ  ተገንብቶለታል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ የተገነባውና የዓድዋን ድል በልኩ የሚዘክረው መታሰቢያ ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ መቆሙንም ተናግረዋል።

የድል መታሰቢያው ለጦር መሪዎችና አርበኞች እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦችን ተጋድሎ ያካተተና እውቅና የሰጠ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የአድዋ ድል በነጻነት እጦትና በጭቆና ሲማቅቁ በነበሩት አፍሪካውያንና በመላው የጥቁር ህዝቦች አዕምሮ ውስጥ ደግሞ ጥቁሮች የማይናቁና ማሸነፍ የሚችሉ እንደሆኑ እምነት በማሳደሩም  ለነፃነት ትግል አነሳስቷል ነው ያሉት።

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው ላደረጉት ትግል ፋና ወጊ መሆኑን በማንሳት፥ ዛሬም ለአፍሪካ አንድነትና ለፓን አፍሪካኒዝም ዓላማ መሳካት የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን የገጠሟቸውን ትንኮሳዎች በድል አድራጊነት የተወጡት በአንድነት፣ በጀግንነትና በሀገር ፍቅር ስሜት በመዋጋታቸው መሆኑን ጠላቶቻችንም ጭምር በሚገባ ያውቃሉ ነው ያሉት።

በመሆኑም እርስ በርስ የሚያጋጩንን ነጠላ ትርክቶች በመፍጠር ከፋፍለው ለማዳከም ባንዳዎችን ቀጥረው የውክልና ጦርነት  ለማድረግ በማቀድ ባለፉት አምስት ዓመታት የውስጥ ግጭቶችን ለማስፋፋት ከፍትኛ ጥረት ስለማድረጋቸው አንስተዋል።

ሠራዊቱን ለማዳከም ብዙ ስራዎች ቢሰሩም ሰራዊቱ ፈተና የሚያጸናው በመሆኑ በአደረጃጀቱ፣ በትጥቁ፣ በስነልቦናውና በአካላዊ ጥንካሬው እየዘመነ ግዳጁን  በብቃት በመወጣት ሴራቸውን ሁሉ ማክሸፉን አብራርተዋል።

"ዛሬም በታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ላይ ለህዝባችን ደግመን ማረጋገጥ የምንፈልገው ጠላቶቻችንን በሚገባ መመከት የሚችል ጠንካራ የመከላከያ ሃይል መገንባታችንን ነው" ሲሉም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፅንኦት ገልጸዋል።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ጠላቶቻችን  ሀገራችንን የማፍረስና ከእድገት ጉዟችን የመግታት ሙከራ እያደረጉ ቢሆንም ፈተናዎችን በድል በመሻገር በርካታ የልማት ውጥኖችን አሳክተናል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ የልማት ሃይል፣ የብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ጋሻና የሀገር መከታ መሆን የሚያስችለውን አቅም ባልተቋረጠ ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሠራዊቱ ዛሬም  የዓድዋ ጀግኖች ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም