የዘንድሮው አድዋ ድል በዓል ታሪኩን በተግባር በሚዘክር ቦታ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው አድዋ ድል በዓል ታሪኩን በተግባር በሚዘክር ቦታ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2016(ኢዜአ)፦የዘንድሮው አድዋ ድል በዓል ታሪኩ በተግባር በሚዘክር ቦታ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናገሩ::
128ኛው የአድዋ ድል በዓል የጥቁር ህዝቦች ድል በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበዓሉ ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የዘንድሮው የአደዋ ድል በዓል ጀግኖች አባቶቻችን ያደረጉትን ተጋድሎ በሚዘክረው አዲስ በተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የዘንድሮ በዓል በንግግርና በስብሰባ ብቻ ሳይሆን ታሪኩን በሚዘክሩ ተሻጋሪ ስራዎች ጭምር በመሆኑ መደሰታቸውንም ተናግርዋል።
ይህን ሃሳብ አመንጭተውና በአጭር ጊዜ ወደ ተግባር ቀይረው ዘመን ተሻጋሪ ስራ ለሰሩ ሰዎች ከፍ ያለ ምስጋናም አቅርበዋል።
መታሰቢያ መገንባት ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን በሚገባ እንዲያጠናና የአርበኝነት መንፈሱ እንዲያድግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
አድዋ ድልም አፍሪካን የመቀራመትን አካሄድ ያከሸፈና ሌሎችን ለትግል ያነሳሳ የይቻላል መንፈስ የፈጠረ ነው ብለዋል።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ በመነሳት የዓለምን ታሪክና ትርክት የቀየሩበት ድል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ድሉ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል መሆኑን ጠቅሰው በጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለማስቀረት የብዙዎችን ዐይን የከፈተ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን ትልቅ ድል የሚዘክር መታሰቢያ መንግስት በአዲስ አበባ መገንባቱ ትልቅ ክብርና ምስጋና የሚያሰጠው ነው ብለዋል።
የአድዋ ድል በዓልን ስናከብር የጦርነቱን ሂደት ሁለንተናዊ ታሪክ በሚገባ ማሳየት ይገባናል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።