ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው - አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር፣ ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር፣ ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር፣ የሀገር ፍቅርንና የአንድነትን እሴቶችን ሸማ የሚያጎናጽፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር ሉዓላዊነትን፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ብሔራዊ ክብርን በጋራ የማፅኛ እሴቶችን ከቀደምት አባቶች እና እናቶች ምግባር እየተማማርን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የዓድዋ ድል ልዩነቶችን በመሻገር ሀገርን የማፅናት አስተምህሮ የሚያስተላልፍልን በመሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመሻገር ትልቁን ምስል ማለትም ኢትዮጵያን የማፅናትና የማበልፀግ ራዕይ ሰንቀን በጋራ ወደ ፊት መራመድ ይኖርብናል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗ ኢትዮጵያዉያን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለብሔራዊ ጥቅሟና ክብሯ ዘላቂነት በጋራ ከመሰለፍ እንዳልገታቸዉ የዓድዋ ድል ህያዉ ምስክር መሆኑን ጠቁመዋል።

የዓድዋ ድልን እሴቶች ስንቅና መርህ አድርገን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መትጋት አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለሕብረ ብሔራዊ ወንድም/እህትማማችነት እሴት ማበብ መሥራት ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ለዚህ ድል ያበቃን ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣ የዓላማ ጽናት፣ መተሳሰብ እና አንድነታችን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ታላቅ ሀገር የአሁኑ ትውልድ ከአያቶቹ የወረሰውን የጀግንነት ታሪክ ጠብቆ ማቆየት እንዳለበትም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

የቀደምት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን የዓድዋ ድል ዐሻራ፣ የዛሬዉን ሀገራዊ ፈተናዎች በማሸነፍ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ለዉጥ እዉን ለማድረግ የብርታትና የፅናት ምንጭ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል ሲሉም አክለዋል።

ሠለማችንን በማፅናት፣ ፀጋዎቻችንን በማልማት፣ ልዩነቶቻችን በሀሳብ የበላይነት መርህ በመዳኘት የኢትዮጵያን ብልጽግና እዉን ለማድረግ በጋራ እንሠለፍ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም