ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በደማቅ ቀለም የጻፈ፤ የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በደማቅ ቀለም የጻፈ፤ የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በደማቅ ቀለም የጻፈ፤ የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል መላ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር በላቀ የሀገር ስሜት፤ ወኔ እና ጀግንነት በማሰባሰብ በተባበረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጣሊያን ወራሪ ኃይል ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ድል ያደረጉበት በዘመን የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ክብር እና ኩራት ያጎናጸፈን የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ድሉ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጎህን የቀደደ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

አባቶቻችን ከልዩነቶች ይልቅ የጋራ ሀገራቸውን በማስቀደም በአንድ ዓላማ ጸንተው በአንድነት እና በጀግንነት ያደረጉት ተጋድሎ ሉአላዊነታችንን ሳናስደፍር በነፃነት እንድንኖር አስችሎናል ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በአል የዐድዋ ድል መታሰቢያ በብሄራዊ ደረጃ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ በዓሉን ይበልጥ ደማቅና ታርካዊ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

መታሰቢያው ሀገራችን ትናንትን የሚያስብ፣ የአባቶቹን አንፃባራቂ ድል በልኩ የሚዘከር እና ከአባቶቹ የአርበኝነት እሴት ወርሶ አርበኛ ለመሆን የሚተጋ ትውልድ ባለቤት መሆኗን ያሳየ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን በአንፃባራቂ ድል የደመቀበት የዐድዋ ድል መታሰቢያ ስናከበር በድሉ እየኮራን የማይቻል ከሚመስለው የአባት የእናቶቻችን የአንድነትና የአልሸነፍ ባይነት የተጋድሎ ታሪክ ትምህርት በመውሰድ በአንድ ልብ ከተነሳን ድህነትን ድል ነስተን ብልጽግናችንን በማረጋገጥ ዳግም አዲስ ታሪክ ከመጻፍ የሚያግደን ምንም ኃይል አለመኖሩን በመገንዘብ ጭምር ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

በመጨረሻ መላው የክልላችንና የሀገራችን ህዝቦች እንደ ሁልጊዜው ለጋራ ቤታችን አንድነት፣ ልማት እና ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ፋይዳ ያላቸው አካባቢያዊና ሀገራዊ የልማት ስራዎች የሚጠበቅባችሁን በማድረግ ዳግም የሀገር አለኝታነታችሁን እንድታስመሰክሩ በአደራ ጭምር ለማሳሰብ እወዳለሁም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም