የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 22/20216 (ኢዜአ)፦የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት ለመላው ለኢትዮጵያ ና ለክልሉ  ህዝብ እንኳን 128ኛው የዓድዋ ድል አደረሳችሁ  የመልካም ምኞት መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነው የዓድዋ ድል በመላው የሀገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው ብሏል።

ጀግኖች አባቶች በአድዋ ጦርነት የውጪ ወራሪን በድል አድራጊነት ያሸነፉት በጀግንነታቸው፣ በአንድነታቸውና በዓላማ ጽናታቸው መሆኑን አስፍሯል።

ጀግኖች አባቶች የውጪ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሀገርን ከድህነት ነፃ ለማውጣት በጽናት እንዲሰራ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል ።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ጽናትን፣ በዘመን የማይሸረሸር ጀግንነትን፣ ክብርን፣ ነፃነት፣ አንድነትንና መሰል ቱሩፋቶችን ያጸና ደማቅ ታሪክ  በመሆኑም የዓድዋን የድል በዓል ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባልም ነው ያለው።

በዓሉን ስናከብርም ሀገራችን የጀመረችው የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር እንዲሁም እርስ በእርሳችን ያለንን አንድነት በማጎልበት አባቶቻችንን ለዚህች ሀገር ሲሉ ለከፈሉት ዋጋ ክብር በመስጠት ሊሆን ይገባል በማለት እክሏል።

ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካም ሆነ የመላ ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ለሆኑ ለአድዋ ጀግኖች ይሁን ሲል መልካም ምኞቹን ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም