ዐድዋ የኢትዮጵያ ልክም መልክም ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ዐድዋ የኢትዮጵያ ልክም መልክም ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለ128ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ዐድዋ ሀብት ነው። አባቶቻችን ያቆዩልን ሀብት። በደም ቀለም፣ በአጥንት ብዕር የተጻፈ ቼክ ነው። እየመነዘርን መጠቀም የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ሆኖ ዘምቶ፣ አንድ ሆኖ ተዋግቶ፣ አንድ ሆኖ ድል አድርጓል። ኅብረ ብሔራዊነቱ በጥበብ፣ በዐቅምና በስልት ልዩ ልዩ መንገዶችን እንዲጠቀም ረድቶታልም ነው ያሉት።

አንድነቱ ደግሞ ለአንድ ዓላማ ዘምቶ፣ ለአንድ ዓላም ተዋግቶ፣ አንድ የጋራ ድል እንዲያገኝ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋል።

ልክነቱ ማናቸውንም ችግሮቻችንን አንድ ሆነን ማሸነፍ እንደምንችል ማሳየቱ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክነቱ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚገባ መግለጡ ነው ብለዋል።

ይሄንን ልክና መልክ ጠብቀንና አልቀን በመጠቀም ኢትዮጵያን ከአድዋ ከፍታ በላይ እንደምናደርሳት እምነቴ ነው ያሉት አቶ ተመስገን

መልካም በዓል ይሁን ሲሉም መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም