እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውም የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል የምናከብረው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሳይሆን ድሉን በሚመጥን መልኩ መታሰቢያ ገንብተን የዓድዋን ጀግኖች እየዘከርን በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን ሁሉ ትተው በአንድነት ሆ ብለው ተነስተው የተዋደቁበት እና የጋራ ድል የተጎናጸፉበት ይህ ታላቅ የድል ታሪክ የአንድነት፣ የመከባበር፣ የፍቅር፣ የጀግንነትና የፅናት ምልክት ሆኖ በወርቅማ ቀለም የተፃፈ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የጋራ ታሪካችን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ታሪክ ለእኛ እና ለመጪው ትውልድ በአንድነት ሀገርን የመጠበቅ የመውደድና ለሀገር ቅድሚያ የመስጠት አደራም ጭምር በመሆኑ፣ በአንድነት፣ በመከባበር፣ በፍቅር፣ በጀግንነትና በፅናት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ዳር በማድረስ የራሳችንን ዘመን የጀግንነት ታሪክ በጋራ እንድንፅፍ ያነሳሳናል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡