የአድዋን ድል በስነ ጥበብ ውስጥ ጉልህ ስፍራ በመስጠት ለአዎንታዊ ትርክት መገንቢያነት ልንጠቀምበት ይገባል

101

ጎንደር  የካቲት 22/2016 (ኢዜአ) የአድዋን ድል በስነ ጥበብና ኪነ ጥበብ ውስጥ ጉልህ ስፍራ በመስጠት ለአዎንታዊ ትርክት መገንቢያነት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር  አመለከቱ ።

"አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ 128ኛው የአድዋ የድል በዓል በጎንደር ከተማ በፓናል ውይይት ዛሬ ተከብሯል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር የትምጌታ ዓለምነህ በፓናሉ ላይ ባቀረቡት ፁሁፍ እንዳሉት የአድዋ ድል ከድሉ ግዝፈትና ካስከተለው ውጤት አንጻር በስነ ጥበብ ዘርፍ የተሰጠው ቦታና ግምት አናሳ ነው፡፡

የአድዋ ድል በፊልምና በሙዚቃው ዘርፍ የተሰጠው ቦታ ከታሪኩ ዓለማቀፋዊነትና ከኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ አንጻር ብዙ መስራትና ማሳወቅ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የስነ ጥበብ ስራዎች የአድዋን ድል ከማጉላትና ታሪካዊ ዳራውንና አሻራውን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገር በማድረግ አብሮነትን፣ አንድነትንና የሀገር ፍቅርን በሚገነባ መልኩ ተደራጅተው መቅረብ እንዳላባቸው ተናግረዋል፡፡

"አሰባሳቢ የጋራ ትርክቶችን ለማጠናከር የአድዋን ድል እንደ ትልቅ ተምሳሌት ልንወስደው ይገባል" ብለዋል፡፡ 

አድዋን የሚዘክሩ የስነ ግጥም፣ የሙዚቃ፣ የስእልና የትያትር ውጤቶች ለጋራ የማንነት እሴቶቻችን ግንባታ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል።


 

ለአድዋ ድል መገኘት የህዝቡ ተጋድሎና መስዋእትነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል። 

''ከእድዋ ድል የጀግኖች አባቶቻችንን አይበገሬነት፣ የዓላማ ጽናት፣ የሀገር ፍቅርና አንድነትን እንማርበታለን'' ያሉት የማእከላዊ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ አቤል መብቱ ናቸው፡፡ 

ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ፈለግ በመከተል ለሀገሩ መከታና አለኝታ በመሆን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመሩ የሰላምና የልማት እቅዶች እንዲሳኩ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ መስፍን አያሌው በበኩላቸው "የአድዋ ድል የኢትዮጵያውን የህብረትና የአንድነት መገለጫ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካችን ውጤት ነው" ብለዋል፡፡ 

የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ የድል ታሪክ ወጣቱ ትውልድ በመጠበቅ የራሱን ደማቅ ታሪክ ዳግም ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡  

ከተሳታፊዎች መካከል ወጣት መንግስቴ መኮንን በበኩሉ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ በመሆኑ መልካም እሴቱን እኛ ወጣቶች ማስጠቀጠል ይገባናል ብሏል፡፡  

የአድዋ ድል በኢትዮጵያ የስነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ የተሰጠው ቦታ በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በበዓሉ አባት አርበኞች፣ ወጣቶችና የመንግስት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም