የአድዋ ድል የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በጋራ መታገል እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ ነው - አምባሳደር ኢቭጌኒ

230

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በጋራ መታገል እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአድዋ ድል መታሰቢያ እንዲገነባ ማድረጋቸው ከኢትዮጵያ ባለፈ ለመላው አፍሪካውያን ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአድዋ ድል በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውጤት ነው። 

በአድዋ የተገኘው ድልም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ይዘው በሌሎች አገራት ላይ ፍላጎታቸውን ለመጫን በሚፈልጉ አካላት ላይ የተገኘ ድል መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በተለይም ድሉ ለአንድ የጋራ ግብ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዱት ትግል የተገኘ ታሪካዊ ድል መሆኑንም ነው የገለጹት። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለአድዋ ጀግኞች መታሰቢያ እንዲገነባ ውሳኔ ማሳለፋቸውና በተግባርም እውን እንዲሆን ማድረጋቸው ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በማድነቅ ለአብነትም አንድነት፣ እንጦጦና ወዳጅነት ፓርኮችን እንዲሁም ሳይንስ ሙዚየም፣ አብርሆት ቤተመጻሕፍት እና በቅርቡ የተመረቀውን የአድዋ ድል መታሰቢያ ጠቅሰዋል። 

እነዚህ ተራማጅ የልማት ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ የተስፋ ምልክቶች ናቸው ብለዋል።

የአድዋ ድልን ለመዘከር የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ጀግኖች መታሰቢያ መሆኑን ተናግረዋል።

መታሰቢያው ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ምን ያክል ወሳኝ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ብለዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን አዲሱን የቅኝ ግዛት አካሄድ መታገል እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባል ብለዋል። 

የዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ሲከበርም ከአሁናዊ ዓለም አቀፍ አውድ አንጻር ትምህርት በመውሰድ ሊሆን ይገባል ብለዋል። 

በተለይም አንዳንድ አገራት የሌሎች አገራትን ሉዓላዊነት በእጅ አዙር ለመጣስ እና በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉ ያሉትን ሙከራ በጋራ ለማክሸፍ የድሉ መከበር ወሳኝ መልዕክት እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ለመላው ኢትዮጵያውያን ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አምባሳደሩ የአድዋ ድል የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም