ፍትኃዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት መኖር በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲረጋገጥ ያስችላል - አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ፍትኃዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት መኖር በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲረጋገጥ ያስችላል - አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት መኖር የተመጣጠነ ዕድገት እንዲረጋገጥና የሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራል የመሰረተ ልማት ፍትኃዊነት ሥርጭት አተገባበር ዙሪያ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከሚኒስትሮችና ከተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት መረጋገጥ የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠያ ዋና ምሰሶ መሆኑ ተጠቁሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት እንዲኖር የክትትል ሥራ እያከናወነ ነው።
በዚህም ጉድለቶች የሚያጋጥሙ ከሆነ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ለፌዴራል ሥርዓት መጠናከርና ውጤታማነት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ግልጽ በሆነ የአሠራር ሥርዓት መመራት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲረጋገጥና የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲኖር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በውይይቱም ስምንት የፌዴራል ተቋማት ፕሮጀክቶቻቸውን በክልሎች እንዴት በፍትሃዊነት እንደሚተገብሩ የተዘጋጀ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎችም ሃሳብና አስተያየት ተሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መሰረተ ልማት ለሁሉም ክልሎች በፍትሃዊነት ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከስምንቱ ተቋማት መካከል ግልጽ መመዘኛና ፍታኃዊነትን ማረጋገጫ ሰነድ ያላዘጋጁ በቀጣይ እንዲያዘጋጁና ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል።
ከኤሌክትሪክ ስርጭት አንጻር ጥሩ መሻሻሎች መኖራቸውን ያነሱት ርዕሳነ መስተዳድሮቹ አሁንም በቀጣይ ተደራሽነት ላይ በሰፊው ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከመንገድ ግንባታ አኳያ ለረጅም ዓመታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ይህን ለማጠናቀቅ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በሌላ መልኩ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን በመስኖ ልማት ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከመንገድ ግንባታ ጋር በተገናኘ ከፕሮጀክት ቁጥር ጋር ብቻ ሳይሆን ከህዝቦች ተጠቃሚነት አንጻር ሊቃኝ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ከትምህርት ተደራሽነት አኳያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማትን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው መሰረተ ልማቶች በሁሉም ክልል ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ከመስኖ መሰረት ልማት አኳያ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ኮንትራቶች ተፈርመው የግንባታ ሂደታቸው እየተከናወነ መሆኑ ተናግረዋል።
የመንግዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱርሃማን የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አዳዲስ ግንባታዎችን ለማከናወንም ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በቴሌኮም፣ በመስኖና በሌሎች ትልቅ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሽመልስ አብዲሳ ፍትሃዊነት የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠያ ዋና ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያከናውኑ ተቋማትን መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።