በዓመት ለኔትወርክ ግዢ የሚወጣውን 60 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

521

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ሀገሪቱ በዓመት ለኔትወርክ ግዢ የምታወጣውን 60 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት የሚያስችል ብሔራዊ የኔትዎርክ ማሳለጫ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለአንድ ሳምንት ሲካሔድ የቆየው ሀገራዊ የዲጂታል አቅሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት'ዛሬ ተጠናቋል።

መርሃ ግብሩ ሀገሪቱ ያላትን የቴክኖሎጂ አቅም አሟጦ ለመጠቀምና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ ነው ተብሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በሚኒስቴሩ የብሔራዊ ኔትወርክ ፕሮጀክት መሪ አቶ ዳንኤል አድነው የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት የሚዳስስ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለው ኢንተርኔት ቨርዠን ፕሮቶኮል አለም የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

በተጨማሪም በቀላሉ መልማት የሚችል የኔትወርክ ስርጭት እያለ ሀገሪቱ ለኔትወርክ ብቻ አላስፈላጊ ወጪ እንድታወጣና ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓቷል ነው ያሉት።

ተግባራዊ የሚደረገው ብሔራዊ የኔትዎርክ ማሳለጫ ፕሮጀክት ሀገሪቱን ከአላስፈላጊ ወጪና ከሳይበር ጥቃት የሚታደግ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን በሙከራ ደረጃ በማልማት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፤ በቀጣይ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ለማድረግ፣ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የተጀመረውን ቴክኖሎጂያዊ አሰራር ለማጠናከርና ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በመሉ ተግባራዊ ሲሆን በዋናነት እየተስፋፋ የመጣውን የሳይበር ጥቃት 80 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

እንዲሁም ለኢንተርኔት ግዢ ሀገሪቱ በዓመት የምታወጣውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ያስችላል ነው ያሉት።

ብሔራዊ የኔትዎርክ ማሳለጫ ፕሮጀክት የተለያዩ የሙከራ ስራዎች ተደርጎለት ስኬታማ በመሆኑ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ በበኩላቸው ሀገራዊ የዲጂታል አቅሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በዲጂታል እና በአይሲቲ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ለማስተዋወቅ የተካሔደ ነው።

በተጨማሪም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሒደት ውስጥ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማስገንዘብና ቴክኖሎጂን አሟጦ ለመጠቀም የሚያግዝ እንደነበርም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የዲጂታል ስርዓቱን ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ግብይቱን ለማስፋትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም