ቀጥታ፡

ከዓድዋ ድል በወረስነው አንድነት ድህነትን ታሪክ ልናደርገው ይገባናል -- ዶክተር ጉቼ ጉሌ 

ሶዶ፣ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)  ከዓድዋ ድል በወረስነው አንድነት ድህንነትን ታሪክ ማድረግ ይገባናል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጉቼ ጉሌ ተናገሩ። 

በዩኒቨርሲቲው "ዓድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ!" በሚል መሪ ቃል 128ኛውን የዓድዋ ድል ቀን ዛሬ ተከብሯል።

ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ቀደምት አባቶች ወራሪና ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ሃይል ድል ያደረጉበት ወኔ ዛሬም ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት ልንጠቀምበት ይገባል። 

በዓድዋ የተመዘገበው ድል የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ ከአፍሪካ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን ገልጸዋል። 

ከዓድዋ ድል በወረስነው የአንድነት ተጋድሎ ታሪክ በመማር ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

አባቶች ወረራውን የጣልያን ሠራዊት ያሸነፉበት የአንድነት ታሪክ፣ አዲሱ ትውልድ ድህነትን ታግሎ በማሸነፍ የራሱን ታሪክ ለማስመዝገብ  ያስችለናል ሲሉም ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሱ የማይሰሩት ታሪክ የለም ያሉት ዶክተር ጉቼ፣ አንድነታችንን በማጠናከር ሀገራችንን ከብልፅግና ማማ ላይ ልናደርስ ያስፈልጋል ብለዋል። 


 

ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያዊያንን የአንድነትና የመተሳሰብ እሴቶቻችንን በማጠናከር ድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል። 

የዓድዋ ታሪክ የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ማሳያ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ታምራት ዴላ ናቸው። 

ድሉ በተባበረ ክንድ የህዝቦችና የሀገር ነፃነት እንዲሁም ክብር ያስጠበቀ መሆኑን አውስተው፣ በየወቅቱ የሚጋረጡብንን ችግሮች በፅኑ አንድነትና መደጋገፍ የማሸነፍ ተሞክሮ ልንወስድ ይገባል ብለዋል። 

በከባድ ፈተናዎች ያለመንበርከክ መንፈስ ከዓድዋ የድል ታሪክ በመጋራት ለችግሮች መፍትሔ አፍላቂ መሆን እንደሚገባ ተመራማሪው ገልጸዋል። 

የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰራዊት ልማት ማህበር የወላይታ ቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት የመቶ አለቃ ታምራት ሞላ የአድዋ ድል በመላው ኢትዮጵያውያን የትብብር መንፈስ የተመዘገበ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም ከድህነት ተላቆ የበለፀገች ሀገር ማፅናት የሚችለው አንድነቱን ጠብቆ ባጋራ መንቀሳቀስ ሲችል ነው ብለዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም