የአድዋ ድል አባቶች የቅኝ ገዥነት ተግባርና አስተሳሰብን ያሸነፉበት ታላቅ ገድል ነው--- ዶክተር ዝናቡ ወልዴ

ዲላ ፤ የካቲት 22/2016 (ኢዜአ)፦ የአድዋ የድል አባቶች የነጮችን የቅኝ ገዥነት ተግባርና አስተሳሰብን ያሸነፉበት ታላቅ ገድል መሆኑን የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ገለጹ።

የዞኑና የጌዴኦ ከተማ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ነዋሪዎች የአድዋ ድል 128ኛ ዓመት  በዓልን ዛሬ በዲላ ከተማ አክብረዋል።

ዋና አስተዳዳሪው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የዘንድሮው የአድዋ በዓል ለጀግኖች አርበኞችና ለድሉ መታሰቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ሙዚየም ተገንብቶ በተመረቀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል።

የአድዋ የድል በዓል አባቶች የነጮችን የቅኝ ገዥነት ተግባርና አስተሳሰብን ያሸነፉበት ታላቅ ገድል መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ምልክት ተደርጋ እንድትታይ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ የአሁኑ ትውልድም የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን አፅንቶ ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

ድሉ ዜጎች ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከተሰለፉ ድል ማድረግ እንደሚችሉ ያስተማረ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ የአሁኑ ትውልድም በአድዋ መንፈስ ተንቀሳቅሶ ለአገራዊ ብልጽግና በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል።


 

አድዋ ኢትዮጵያዊያን የዘር አድልዎንና ኢ-ፍትሐዊነትን አምርረው የታገሉበት ደማቅ የድል በዓል ነው ያሉት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሺፈራው ናቸው።

በጦርነቱም ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት የመጣውን ጦር ድል በማድረግ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ያደረገ ታሪክ መመዝገቡን አስርደተዋል።

በጦርነቱ የተሳተፉ አባቶች የሀገርን ነፃነትና አንድነት በማስቀጠል ለዛሬው ትውልድ ክብሯ የተጠበቀ ሉአላዊት አገር ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድም ድህነትንና ኋላቀርነትን አምርሮ በመታገል በአባቶች ደምና አጥንት ጸንታ የቆየችውን አገሩን ወደ ብልፅግና ማሸጋገር ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል።

የበዓሉ ተሳታፊ አባት አርበኛ ሃይሉ በየነ በበኩላቸው ወጣቱ ትውልድ ደማቁን የአባቶቹን ገድል ከመዘከር ባለፈ፣ አገርን ከፍ የሚያደርግ የራሱን አኩሪ ታሪክ እንዲሰራም አሳስበዋል።

በተለይም  ሀገራዊ አንድነቱን ጠብቆ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ እንዲቆምም ጠይቀዋል። 

ወጣት ስጦታው ተረፈ በሰጠው አስተያየት ''አባቶቼ ወራሪውን ሃይል ድል ያደረጉበትን በዓል የማከብረው በተሰማራሁበት የሥራ መስክ ጠንክሬ በመስራት ደማቁን የአድዋ ድል በልማት በመድገም ነው'' ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም