ቀጥታ፡

በ75 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር አገር አቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ በ75 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር አገር አቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ ።

ፕሮጀክቱ በጣሊያንና ኔዘርላንድ እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የግብርና፣የጤና፣የትምህርት፣የፕላንና ልማት ሚኒስትሮች እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በተቀናጀ መልኩ ይተገብሩታል ተብሏል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታው አብርሃም አዱኛ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በአግባቡ ተጠቅማ ለዘላቂ ልማትና ዕድገት እንድታውል የተፋሰስ አካባቢዎችን ማልማት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የውሃ ሃብትን ከብክለትና ከብክነት ተከላክሎ በተቀናጀ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋልና አደጋዎችን ለመቀነስ ተፋሰስ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የጣሊያንና የኔዘርላንድ መንግስታት ለኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር እንዲኖር የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት  የአጋር አካላት ድጋፍ ያልተገኘባቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነውና ለአምስት ዓመታት ይተገበራል የተባለው አገርአቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክትም ተፋሰሱን በማልማት የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ  በአዋሽ፣ አባይ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ተከዜ፣ ዋቢ ሸበሌና በዳናኪል ተፋሰሶችን በማልማት የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ዳይሬክተር ጌቴ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያጎናጸፈቻትን የውሃ ሃብት በአግባቡ ተጠቅማ ለዘላቂ ልማት እንዳታውል በርካታ እንቅፋቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

አገሪቱ ከዝናብ ከምታገኘው ውሃ 40 በመቶ የሚሆነውን በጎርፍ እንደምታጣና ይህን የውሃ ብክነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ጎርፍና ድርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

ውሃን በአግባቡ በመያዝ ለልማት ማዋል የሚቻለው ዕውቀት መር የሆኑ ስራዎችን በመስራትና ተፋሰሶችን ማልማት ሲቻል መሆኑንም አንስተዋል።


 

በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ የልማትና ትብብር ሃላፊ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን  በአግባቡ ተጠቅማ ለዘላቂ ልማቷ እንድታውል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም