የአድዋን የጀግንነትና የአሸናፊነት መንፈስ አገራዊ ልማትን በማረጋገጥ መድገም ይገባል--- አርበኞች

102

ሀዋሳ እና አርባ ምንጭ ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ከአድዋ ድል የሚቀዳውን የጀግንነትና የአሸናፊነት መንፈስ አገራዊ ልማትን በማረጋገጥ መድገም እንደሚገባ ኢዜአ በሀዋሳና በአርባ ምንጭ ከተሞች ያነጋገራቸው አርበኞች ገለጹ።

ኢትዮጵያዊያን ከአራቱም ማዕዘን ተሰባስበው የቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት በእብሪት ተወጥሮ የመጣውን የጣልያን ጦር ድል መተው ደማቅ ታሪክ ከጻፉ ነገ 128 ዓመት ይሞላቸዋል።

ጀግኖች አባታች፣ አያቶችና ቅድመ አያቶቻችን በአንድነት በከፈሉት የደምና አጥንት መስዋዕትነት ድል ከማስመዝገብ ባለፈ ሉአላዊነቷ ተከብሮ የቆየች ኢትዮጵያን አስረክበውናል። 

የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል የሆኑት ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡት የአድዋ ድል ለትውልዱ ከጀግንነት ባለፈ የአሸናፊነት መንፈስን ያላበሰ መሆኑን በሃዋሳና በአርባ መንጭ ከተሞች ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አርበኞች ገልጸዋል።    

አርበኞቹ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም ማዕዘን በአንድነት እና በሀገር ፍቅር ስሜት ተነስተው ለመላው የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የሆነ ድል በአድዋ ተራሮች ላይ አስመዝግበዋል።

የጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ የኋላሸት ቸርነት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያዊያን በጋራ መስዋዕት የከፈሉበት የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ፈር የቀደደ የነጻነት ተምሳሌት ነው።

ጀግኖች አባቶችና አያቶቻቸን በወቅቱ በዘር፣ በሀይማኖትና በቋንቋ ልዩነት ቢኖራቸውም ለአገር ቅድሚያ በመስጠት የአንድነት ታሪክ ሰርተው ነጻ ሀገር ያስረከቡንን ትውልዱ ሊማርበት ይገባል ብለዋል።

አርበኛው እንዳሉት የአድዋ ድል ነጮች በጥቁር አይሸነፉም የሚለውን እሳቤ የተቀየረበትና ኢትዮጵያንም በዓለም መድረክ ከፍ ያደረገ አኩሪ ደማቅ ታሪካችን ማሳያ ነው።

ወጣቱ ትውልድ የአድዋን የአሸናፊነት መንፈስ አገርን በማሳደግ መድገም እንዳለበትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በከፋፋይ ሀሳብ ወደግጭት እንድንገባ የሚጠነስሱትን ሴራ በተለይ ወጣቱ ተረድቶ ለአገር ሰላም፣ እድገትና እንድነት በጋራ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ የአርበኞች ማህበር ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አባል ወይዘሮ ምንታምር ደርሰህ በበኩላቸው፣ “ጀግኖች አባቶቻችን ይህችን ሀገር በጋራ ቆመው ነው ያጸኗት" ይላሉ።

ወጣቱ እንደጀግኖች አባቶች አገሩን ከምንም በላይ በማስቀደም ከፋፋይ እሳቤን ከውስጡ በማውጣት ኢትዮጵያን የማስቀጠል ግዴታውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።     

አድዋን በየዓመቱ ቀኑን ጠብቆ ከማክበርና ሰማዕታትን ከመዘከር ባለፈ ቋሚ የሆነ መታሰቢያ እንዳልነበረው የተናገሩት አርበኛዋ፣ መንግስት ይህን አስቦ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባቱ ትውልዱ የአባቶቹን ታሪክ በተጨባጭ እንዲያውቅ ያግዘዋል ብለዋል።

ወጣቱ የአድዋን የጀግንነትና የአሸናፊነት መንፈስ አገራዊ ልማትን በመራጋገጥና የራሱን አኩሪ ታሪክ በመስራት መድገም እንዳለበት ወይዘሮ ምንታምር ተናግረዋል። 

"ሁሉም ጦር ሜዳ መሄድ ሳያስፈልገው በተሰማራበት የሙያ መስክ ውጤታማ በመሆን ለሀገሩ አርበኛ መሆን አለበት" ብለዋል።


 

የጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ገመዳ እንዳሉት፣ ጥንት አባቶቻችንና አያቶቻችን ለሀገራቸው ነፃነት በዱር በገደሉ ተዋድቀው ለዓለም የጥቁር ህዝቦች ቀንዲል የሆነችውን ኢትዮጵያን ከነክብሯ በማቆየት ታሪክ ጽፈዋል።

በዘመናዊ መሣሪያ ተደራጅቶና በእብሪት ተወጥሮ የመጣውን የቅኝ ገዥ ጠላት ድል ማድረግ የቻሉበት ምስጢር አንድነታቸውን መጠበቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ትውልድ ከጥንት አርበኞች ጽኑ የሀገር ፍቅርና አንድነት ተምሮ ኢትዮጵያን በልማት ለመለወጥ በሚሰሩ ሥራዎች አሻራውን ማኖር እንዳለበት ተናግረዋል።

የአድዋ አባቶችን የከፍታ ታሪክ ሰርቶ ድህነትን በማሸነፍና አገርን በማሳደግ መድገም የትውልዱ አደራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም