የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን ትምህርት የሚሰጥ የታሪክ አሻራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ የታሪክ አሻራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

አድዋ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርኃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት በተባበረ ክንዳቸውና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸው ወራሪ ኃይልን አንበርክከዋል ብለዋል።

የአድዋ ድል በህብር፣ በፍቅርና በትብብር የተገኘ ግዙፍ ድል መሆኑን ጠቅሰው፥ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጦር በህብረ ብሔራዊ አንድነት የተዋቀረ ሃይል መሆኑንም አንስተዋል።

በአድዋ ዘመን የታየው የሀገርና የወገን ፍቅር ዛሬም ፀንቶ እንዲቀጥል መሥራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ከምንም በላይ ነው ብለዋል።

የአድዋ ዘመን ጀግኖች የተለያየ ቋንቋ እየተናገሩ፣ የተለያየ ሃይማኖት እየተከተሉ፣ በአንድነት የዘመቱት ለሀገር ከመተባበር የሚበልጥ ነገር እንደሌለ ስለተገነዘቡ መሆኑንም አብራርተዋል።

አድዋ ሀገር የሚታደግና የሚያጸና ትምህርት ቤት መሆኑን ጠቅሰው፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል።

የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፥ ኢትዮጵያውያን በታሪክ አጋጣሚ ግፈኞች የሰነዘሯቸውን ትንኮሳዎች በድል አድራጊነት መቋጨታቸውን የአድዋ ድል ህያው ምስክር ነው ብለዋል።


 

አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሠላም መድረኮች ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላሟ የበዛ እና ብልፅግናዋ የተረጋገጠ እንድትሆን የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማገዝ ነው ብለዋል።

አድዋ የአንድነታችን ሰንሰለት፣ የነፃነታችን ሰንደቅ የጀግንነታችን ልህቀት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ድሉ የአንድ ዘመን ክስተት ብቻ ሳይሆን ትውልዱ የሚማርበት የጀግኖች አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።

ትውልዱ ኢትዮጵያን ለችግር የዳረጋትን መጥፎ የፖለቲካ ባህል ከመገዳደል ወደ መደራደር በመቀየር የራሱን የአድዋ ድል ሊያበስር እንደሚገባ መክረዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለመላ ጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነ ድንቅ የታሪክ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግም የዛሬው ትውልድ፤ ከትናንት የአድዋ ጀግና አያቶቹ ትብብርና አንድነት ትምህርት ሊወስድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የአድዋ ድል ታሪክ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ግንባታ በብልሃት፣ በጥንቃቄና በትዕግስት ዕውን ለማድረግ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵን ህልውና የሚፈታተኑ ግጭቶችን መፍትሔ በመስጠት ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ምሁራን ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ወጣቶች ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነትን ማስቀደም አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምሁራንም በዕውቀት ላይ ተመሰረተ ሃሳብ ያለው ዜጋ በማፍራት ቀጣዩን ትውልድ ማነጽ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩም የታሪክ ኢምሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ "አድዋና ፓን አፍሪካኒዝም" እንዲሁም ፕሮፌሰር መስፍን ዓርአያ "አድዋ ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገር ግንባታ" በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽሁፍ አቅርበው ምክክር ተካሂዷል።

128ኛው የአድዋ ድል በዓል ነገ ቅዳሜ የካቲት 23/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም