ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስጠበቀ የዓድዋ ጀግኖች ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

82

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራርና አባላት ዛሬም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስጠበቁ የዓድዋ ጀግኖች ልጆች መሆናቸውን በተግባር እያስመሰከሩ ይቀጥላሉ ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በሚታተመውና 128ኛውን የዓድዋ ድል በማስመልከት "አድዋ-ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ ውርስ" በሚል በተዘጋጀው መከታ መፅሔት ልዩ ዕትም ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ የድል በዓልን የምታከብር አፍሪቃዊት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ይህም የሆነው የሀገር ነጻነትን ለማስከበር ማንኛውንም ዋጋ የከፈሉና ለመክፈል የተዘጋጁ የጀግኖች ህዝቦች ሀገር በመሆኗ ነው ብለዋል።

ከኢትዮጵያ የድል አድራጊነት ታሪኮች ውስጥ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው ዘመናዊውን የፋሽስት ወራሪ ሠራዊት በአፍሪካ ምድር በማሸነፍ ደማቅ ታሪክ የተጻፈበት የዓድዋ ድል መሆኑን ገልጸዋል።

ድሉ ትልቅነቱን የሚመጥን ዋጋ ሳይሰጠው በየዓመቱ ለትውስታ ብቻ እየተከበረ ቆይቶ፥ በዚህ ትውልድ ያማረ እና ታሪኩን በተሟላ ሁኔታ የሚዘክር የድል መታሰቢያ ተግንብቶለታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብት፣ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ግዙፍ ታሪኳ ምክንያት ምንጊዜም በክፉ የሚመለከቷት የውጭ ጠላቶች መኖራቸውንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አንስተዋል።

እነዚህ ጠላቶች ድንበር ጥሰውም ሆነ የኢትዮጵያን ሰራዊት ፊት ለፊት ተዋግተው እንደማያሸንፉ ያውቁታል ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፥ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ሞክረው አሳፋሪ ሽንፈት መከናነባቸውን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በወኔ፣ በጀግንነትና በፅናት ተዋግቶ ወራሪን በማሸነፍ አንፅባራቂ ድል ማስመዝገቡን ጠቅሰው፥ ድሉ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ተከፋፍለው የቅኝ ገዥ የበላይነታቸውን ዘላለማዊ የማድረግ ውጥን የነበራቸውን ሃይሎች ክፉኛ ያስደነገጠ ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው ላደረጉት ትግል ፋና ወጊ መሆኑን በማንሳት፥ ዛሬም ለአፍሪካ አንድነትና ለፓንአፍሪካኒዝም ዓላማ መሳካት አትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች እርስ በርስ የሚያጋጩንን ነጠላ ትርክቶች በመፍጠር ከፋፍለው ለማዳከም ባንዳዎችን ቀጥረው የውክልና ጦርነት ለማድረግ በማቀድ ባለፉት አምስት ዓመታት የውስጥ ግጭቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ስለማድረጋቸው አንስተዋል።

ሠራዊቱን ለማዳከም ያልፈነቀሉት ነገር እንደሌለ በማንሳት፥ ሆኖም ሰራዊቱ ፈተና የሚያጸናው በመሆኑ በአደረጃጀቱ፣ በትጥቁ፣ በስነልቦናውና በአካላዊ ጥንካሬው እየዘመነ ግዳጁን በብቃት በመወጣት ሴራቸውን ሁሉ ማክሸፉን አብራርተዋል።

"ዛሬም በታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ላይ ለህዝባችን ደግመን ማረጋገጥ የምንፈልገው ጠላቶቻችንን በሚገባ መመከት የሚችል ጠንካራ የመከላከያ ሃይል መገንባታችንን ነው" ሲሉም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፅንኦት ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሠራዊት በዓለም አቀፍ፣ በአህጉሪቱና በቀጣናው ሰላምን በማስከበርና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ወሳኝ ሃይል መሆኑን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብም የቅርብ ጎረቤቶችም በሚገባ እንደሚያውቁት አንስተዋል።

ሠራዊቱ በከፈለው መስዋዕትነት ከራሱ አልፎ የጎረቤት ሀገራትን ሀገረ መንግስት ማፅናቱን በመጠቆም።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እያደረገች ያለችው የባህር በር የማግኘት ጥረት ሲሰምር፥ ሠራዊቷ ለቀጣናዊና አካባቢያዊ ሰላም የሚጫወተው አወንታዊ ሚና ከፍ እንደሚልም ገልጸዋል።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ የልማት ሃይል፣ የብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ጋሻና የሀገር መከታ መሆን የሚያስችለውን አቅም ባልተቋረጠ ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ ሠራዊቱ ዛሬም የዓድዋ ጀግኖች ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይቀጥላል ብለዋል።

መከታ 2ኛ ዓመት ልዩ ዕትም መፅሔት ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መልዕክት በተጨማሪ የባሀር በርን በማስመልከት ከአምባሳደር ባጫ ደበሌ ጋር የተደረገ ቃለመጠይቅ፣ ቀይ ባህርና የዓድዋ ጦርነት፣ የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊነት፣ የኢትዮጵያ የባህር ሃይል ትልዕኮና ዝግጁነት፣ በ36 ሰዓታት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ስልተጠናቀቀው የዳኖት ውጊያና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን አካቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም