ለዓድዋ ድል የሴቶችን ጥበብ የተሞላበት አስተዋጽኦ ሰላምና ልማት ግንባታ ላይ  ልንተገበረው ይገባል- የባህር ዳር ከተማ  ሴቶች

ባህር ዳር ፤ የካቲት 22 /2016 (ኢዜአ)፡- ለዓድዋ ድል ሴቶች ያሳዩትን ጥበብ የተሞላበት አመራር በአርአያነት ወስደን ሰላምና ልማት ግንባታ ላይ  ልንተገብረው ይገባል ሲሉ በባህር ዳር ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ሴቶች  ገለጹ።

128ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በዓድዋ መታሰቢያ ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

ከባህርዳር ከተማ ነዋሪ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ትግስት ጌታቸው እንዳሉት፤ቀደምት እናቶች ስንቅ በማዘጋጀትና በማቀበል፣ተዋጊ ኢትዮጵያዊያን አበረታች ድጋፍና አመራር በመስጠት ለዓድዋ ድል ታሪክ ሰርተው አልፈዋል።

ይህም የሴቶችን የአይችሉም መንፈስ የሰበረና በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ እኛም የዛሬው ትውልድ  አርአያነታቸውን ልንከተል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ዛሬም በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በውትድርናው መስክ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና ለአገራቸው አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ሴቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን ጀግንነት እየሰሩ ያሉ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ለሀገር ጥቅምና ሉዓላዊነት መከበር የተረጋጋ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት ፤ ለዚህም ባሎቻችን፣ ልጆቻችንና ወንድሞቻችን ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ መምከርና ማስተማር ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዓድዋ ድል ጊዜ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች እናቶችን ከመዘከር ባለፈ ወቅቱ የሚጠይቀውን ታሪክ መስራት እንደሚያስፈለግ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መብራት ይርሳው ናቸው።

ዛሬ አገር ከሴቶች የምትፈልገው ስለ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲሰሩ ብሎም እንዲያሰሩ ለሌሎችም በአርአያነት  መታየት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሴቶች ከወንዶች እኩል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥና የችግሮች መፍቻ ቁልፍ እንደሆኑ የዓድዋ ድል ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእነዚያ ጀግኖች መንፈስና ወኔ መላበስ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወይዘሮ አታሌ ነጮ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ሴቶች የህይዎት መስዋትነት በመክፈል ለአገር ሉዓላዊነት መከበር የድርሻቸውን እንደተወጡ በታሪክ ሲወሳ እንደቆየ አስታውሰዋል።

“ሴቶች በተፈጥሮ ተደማጮችና የመፍትሄ አካሎች ነን” ያሉት ወይዘሮ አታሌ ፤ ታሪካዊው የዓድዋ ድል ተሳታፊ እናቶች ተጠቅመውበታል ብለዋል።

ለዓድዋ ድል ሴቶች ያሳዩትን ጥበብ የተሞላበት አመራርና ቁርጠኝነት በአርአየነት ወስደው ለአገር ሰላምና ልማት ግንባታ እንዲውል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ትናንት በባህር ዳር ከተማ  በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን በወቅቱ ተገልጿል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም