ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶችን በማስተላለፍ ዙሪያ የሚታዩ የአሰራር ክፍቶችን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ ነው

90

 አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ከአገራዊ ለውጡ ጀምሮ ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶችን በማስተላለፍ ዙሪያ የሚታዩ የአሰራር ክፍቶችን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራል ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች የ2015 በጀት ዓመት ትልልፍ የእቅድ አፈጻጸም ላይ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ይገኛል።  

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ፤ ውስን ዓላማ ካላቸው የድጎማ በጀት ትልልፍ አንጻር እስከ አገራዊ ለውጡ ድረስ ተጨባጭ የሚባሉ ተግባራት ያልነበሩ መሆኑን ገልፀዋል።  

በፌዴራል ሥርዓት የመንግሥታት ግንኙነቶች አንዱ የበይነመንግሥታት የፊስካል ግንኙነት መሆኑን በማንሳት ይህም ዋና ዓላማው ኃብት ከፌዴራል መንግሥት በየደረጃው ላለው የመንግሥታት እርከን በፍትኃዊነትና በውጤታማነት ማስተላለፍ መሆኑን ገልፀዋል።  

በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች የጋራ የጥቅል ድጎማ በጀት የሚያከፋፍልበትን የቀመር ሥርዓትን አስጠንቶ ሲወስንና ተግባራዊነቱን ሲከታተል መቆየቱን ገልፃዋል። 

ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ የኃብት ክፍፍል ፍትኃዊነት ለማረጋገጥ የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚያስችለውን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል:: 


 

በዚህም ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶችን በማስተላለፍ ዙሪያ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት የተወሰነ ዓላማን ለማሳካት ስለሚደረግ የድጎማ በጀት የክትትል ሥርዓትን ለማስፈጸም ደንብ ቁጥር 05/2014 ዓ.ም በማውጣት ወደ ሥራ መግባቱን ገልፀዋል። 

በዚህም በጀት ሰጪ ተቋማቱ የትልልፍ መስፈርት አዘጋጅተው ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለክልሎች ማስተላለፍ እንዳለባቸው በመግባባት ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት። 

በዛሬው መድረክም በ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ክልላዊ የትልልፍ መስፈርትን መሠረት አድርጎ ስለመፈጸሙና እንደ ተቋማቱ ባህሪ አንፃር ስለመቃኘቱ በግልፅ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል።  

በመድረኩ የ2015 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የተላለፉ ጠቅላላ የድጎማ በጀት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል:: 

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት 40 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በተቋማት የተላለፈ ውስን አለማ ያላቸው ድጎማዎች፣ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጥቅል አላማ ላለው ድጎማዎች እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች የተከፋፈሉ መሆኑም ተገልጿል። 

ውስን ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች በክልሎች የሥልጣን ወሰን ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ለማስፈጸም ከፌዴራል መንግሥት በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት ወደ ክልል መንግሥታት የሚተላለፉ የድጎማ ዓይነቶች ናቸው:: 

በመድረኩ ባለድርሻ አካላት ከተወያዩ በኋላ ምክር ቤቱ ግልፅ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም