ሴቶች ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል 

ደብረብርሀን ፤ የካቲት 22/ 2016  (ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ ሴቶች  የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ  እንደሚገባ  የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አስገነዘቡ ።

በደብረ ብርሃን ከተማ “ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ “ በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዛሬ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የነበረው የጸጥታ ችግር ተወግዶ አሁን ላይ ለሰፈነው ሰላም የሴቶች ሚና ከፍ ያለ ነው።

የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረዊና ፖለቲካዊ  ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዞኑ አሁን ያለው ሰላም ወደ ዘላቂነት እንዲሸጋገር የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል። 

የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ የሮምነሽ ጋሻው በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ስናከብር ተጠቃሚነትና ተሳታፊነታችንን ለማሳደግ መሆን አለበት ብለዋል ።

በህዝቦች መካከል ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን የመከባበርና የአንድነት እሴት በማስጠበቅ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በቅንጅት መስራት አለብን ሲሉ አክለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በሴት ህጻናት ላይ የሚፈጸመውን አስገድዶ መድፈርና ያለእድሜ ጋብቻ ለማስወገድ ከህግ፣ ከሃይማኖት አባቶችና ሌሎች አካላት ጋር በመተባበር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዞኑ ከአንጎለላና ጠራ ወረዳ የመጡት የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ምንዳ ሰብስቤ  በአካባቢያችን የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት በኩል ሀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል ።

የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት እንዲጎለብትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንሰራለን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ  አልማዝ  ታምሬ ናቸው ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም