የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው - ወይዘሮ አየለች እሸቴ

ድሬደዋ ፤ የካቲት 22/2016 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ቤት የምገባ መርሃግብር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በማሳደግ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን  የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ገለጹ።

"ለአገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ ለተሻለ ትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ለ9ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ በድሬዳዋ ዛሬ ተከበሯል።

ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በዚሁ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልል መንግስታት፣ በአጋር ድርጅቶችና ማህበረሰቡ ተቀናጅቶ ባደረገው ርብርብ በ2013 ዓ.ም ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

ዘንድሮም መርሃግብሩን በተቀናጀ መንገድ ተደራሽ በማድረግ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በድሬደዋ በገጠርና በከተማ የተጀመረው የትምህርት ቤት የምገባ መርሃግብር በችግር ሳቢያ ከትምህርት ገበታ የሚለዩ ህፃናት በትምህርታቸው በርትተው እንዲማሩ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለስራው መሳካት በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እንዲሁም ባለሃብቶችና ማህበረሰቡን በማስተባበር የተካሄደው ዘመቻ መሠረታዊ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

ለመርሃ ግብሩ መሳካት አስተዋፅኦ እያደረጉ የሚገኙትን ባለድርሻ አካላት አመስግነው የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዘንድሮ አስተዳደሩ በመደበው 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ በአራት የገጠር ክላስተር የሚገኙ 6 ሺህ 430 በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬደዋ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ናቸው።


 

እንደ ቢሮው ኃላፊ ገለፃ ከአስተዳደሩ በተጨማሪ ሁለት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በከተማና በገጠር ለሚገኙ 4 ሺህ 740 ተማሪዎች የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር እይተካሄደ ይገኛል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ በድሬደዋ አዲስ ከተማና በገጠር ትምህርት ቤቶች በመገኘት የተማሪዎች የምገባ ስራዎች ተጎብኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም