አድዋ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ወሳኝ ድል ነው - ጁሊየስ ጋርቬይ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ድል ነው ሲሉ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ታጋይ የነበረው የማረከስ ጋርቬይ ልጅ ጁሊየስ ጋርቬይ (ዶ/ር) ተናገሩ።  

ዶክተር ጁሊየስ ጋርቬይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ላይ በአድዋ የተቀዳጀችው ድል በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል።  

ድሉ ኢትዮጵያ እንዳትገዛ  ከማስቻሉም በዘለለ የጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው እንዲነሳሱ ምክንያት መሆኑን  ገልጸዋል።    

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ትልቅ ሥፍራ እንዳላት ተናግረዋል። 

የአድዋ ድል ከአፍሪካ ውጪ በሚገኙ የጥቁር ሕዝቦች መካከል የፓን-አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ  በማነቃቃት በኩልም ትልቅ ሚና እንደነበረው አብራርተዋል።

በመሆኑም ይህንን ታሪክ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካቶ በማስተማር ለአዲሱ ትውልድ ያለፈውን ታሪክ  በተገቢው ሁኔታ ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት ባለመንበርከክ ያስመዘገበችውና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምሳሌ በመሆኑ የአድዋ ድል ሁሉም ጥቁር ሕዝብ የሚያከብረው መሆኑን ተናግረዋል። 

ማርከስ ካርቬይ የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ታጋይና የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ከነበራቸው ጥቂት ግለሰቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።  

ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል በአንድነት ተሰልፈው ድል ያደረጉበት 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በነገው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም