በመጪው ሰኔ 6 በአራት ክልሎች ለሚካሂደው ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ ፤የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦በመጪው ሰኔ 6 በአራት ክልሎች ለሚካሂደው ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና የሲቪክ ማኅበራት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ 6ተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ በሆነ መልኩ ተካሂዷል። 


 

ይሁን እንጂ በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ በተለያዩ ምክንያት ማካሄድ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ቦርዱ 6ኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸውና በቦርዱ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ እንዲደረግባቸው በተወሰኑ ሥፍራዎች ሰኔ 6/2016 ዓ.ም ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።

ምርጫው በ4 ክልሎች ማለትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም 9 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና 26 የክልል ምክር ቤት ተወካዮችን ለመምረጥ ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል። 

የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ብሩክ ወንድወሰን በበኩላቸው የ6ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ የድምፅ መስጫ ቀን ሰኔ 6/2016 ዓ.ም መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሰኔ 6 እና 7 2016 ዓ.ም  የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ይፋ የሚደረግበት ቀን ነው ብለዋል። 

ሰኔ 16 2016 ዓ.ም ቦርዱ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ይፋ የሚደረግበት ጊዜ መሆኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የፓርቲ ተወካዮችና የሲቪክ ማኅበራት አባላት ሰኔ 6 ቀን 2016 የሚካሄደው ምርጫ ተገቢ መሆኑን አንስተው ምርጫው ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

እንዲሁም ምርጫ ለማካሄድ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ የሥራ ቀን ላይ ስለሚሆን ቅዳሜ ወይም እሁድ እንዲሆን ኃሳብ አቅርበዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም