ሴቶች - የአድዋ ድል ሁለንተናዎች

2427

                                    ሴቶች - የአድዋ ድል ሁለንተናዎች

                                                 በአየለ ያረጋል

"... መጨረሻም ድምሩን ስገምተው አድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎዎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል..."

ይህን ያሉት ታላቁ ምሁር እና የአድዋ ዘማች ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማርያም ናቸው። በርግጥ በአድዋ ዘመቻ ያልዘመተ የለም። የሀይማኖት መሪዎች፣ ንጉሱ፣ ንግስቲቱ፣ ገበሬው፣ አገሬው ከነማንነቱ… ገድል ፈጽሟል። 

በጦር ሜዳ ገድሎች የሴቶች አበርከቶ እምብዛም አይታወስም። ሴቶች የዋሉበት ግንባር አይዘከርም። ቅሉ ሴቶች በኪነ-አድዋ ያልተዘመረላቸው ‘’ደብዛዛዎቹ ጀግኖች” ናቸው። እቴጌ ጣይቱን መሰል የአድዋ ሴት የጦር ፊታውራሪዎች አሉ። አዝማሪ ጣዲቄና መሰል አዝማሪዎች የሰራዊቱ ስነ ልቦና ገንቢዎች ናችው። ሴቶች የሎጂስቲክስ አሳላጮች፣ የቁስለኛ ሀኪሞች፣ የጀግና አበርቺዎች፣ የስንቅ ሰናቂዎች፣….በጥቅሉ ሴቶች የአድዋ ድል ሁለንተናዎች ነበሩ።

ለዚህ ደግሞ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ቀዳሚ ምስክር ናቸው። እቴጌ ጣይቱ ከውጫሌ እስከ መቀሌ፣ ከእንጦጦ እስከ ማርያም ሸዊቶ መላ መቺም፣ ጦር አዝማችም ነበሩ።

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዜና መዕዋል ከታቢ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደአረጋይ ‘ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ’ በተሰኘው መጽሐፋቸው የሴቶችን ሚና በተመለከተ እንዲህ ይላሉ። 

“እንዲህም እየሆነ፣ አጤ ምኒልክ ባዳራሹ እቴጌ ጣይቱ በእልፍኝ ባለሟሎችን ወይዛዝርቱን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል፣ ይዘምታሉ። ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ፣ ስለምንድነው ያልህ እንደሆነ ይህን ታሪክ መመልከት ነው። በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፣ በአራት ድንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ በኮዳ ደግሞ ሦስት መቶ ስድስት መቶ የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ግብሩ ይጎድል ይመስልሀል” (ገጽ-241)

 ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ይቀጥላሉ። 

“… ጥቂቱን ጻፍን እንጅ በአድዋ ጦርነት ዐይናቸን እንዳየው ጆሯችን እንደሰማው መጻፍ አይቻለንም። እቴጌ በዚያን ጊዜ በግምባርዎ ተደፍተው በጉልበትም ተንበርክከው ድንጋይ ተሸክመው እግዚአብሄር እያመለከቱ ሲያዝኑ ሲጨነቁ ነበር። … ሴት ወይዛዝርቱም የንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ወይዘሮ ዘውዲቱም ደንገጡሮችንም ተከትለው ነበር። የኋላው ሰልፈኛ እንደመወዝወዝ ሲል ባዩ ጊዜ ቃልዎን አፈፍ አድርገው ተናገሩ። አይዞህ አንተ ምን ሆነሃል! ድሉ የኛ ነው በለው! አሉት… ጣሊያ ድል ከሆነ በኋላ ወንዱ በርኮር፣ ሴቱ በገንቦ ውሃ ያዙ ብለው አዘው ለተጠማውና ለቆሰለው ውሃ ሲያጠቱት ዋሉ። እንኳን ኢትዮጵያ ሰው የኢጣሊያው ስንኳ ቁስለኛ ከዚያ ስፍራ የተገኘ ከዚህ ከእቴጌ ካዘዙት ውሃ አልቀረበትም“ይላሉ። 

ከጽሁፉ መረዳት እንደሚቻለው እቴጌ ጣይቱና መሰሎቻቸው አንድም በጸሎታቸው፣ አንድም ተዋጊዎችን በማደፋፈር ወኔያቸው፣ አንድም በጦር መሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል። ዋናው ደግሞ ቁስለኞችን የማከምና ሰብዓዊነት ሙያቸው ነው።  

ፀሃፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ “… ሙሉ ግብር እየበላ የተጓዘ እንጂ ወታደር የስንቅ አቁማዳዉን አልፈታም“ ሲሉ የአድዋ ሴቶች ገድል ምንኛ ገናና እንደሆነ መገመት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ። እንደ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ስለዘመቻው አጓኳን በማስታወሻቸው እንደገለጡት ድንኳን ተካይ፤ ዕንጨት አቅራቢው፣ ወጥ ሰሪው፣ እንጀራ ጋጋሪው፣ እህል ውሃ ተሸካሚው፣ መልከኛው (አራጁ)፣ በቅሎ ጫኙ፤ ተዋጊው ሁሉም በየፊናው እንስሳቱም ሳይቀር ተደራጅቶ ዘምቷል። 

በርካታ የታሪክ ምንጮች የአድዋ ጦርነት ተሳታፊዎች ገሚሶቹ ሴቶች እንደሆኑ ይገልጻሉ።  የታሪክ ምሁሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ ደግሞ በአንድ ወቅት ሚዲያ ላይ ቀርበው “በአድዋ ጦርነት ዘማቾች 75 በመቶ ሴቶች ነበሩ” ብለው ነበር። በአድዋ ጦርነት ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች ተመድበው ከካምፕ እስከ ጦር ሜዳ ከመመገብ እስከ ማጀገን፣ ከማከም እስከ መዋጋት ድንቅ ሚና ተወጥተዋል። ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት ይዘው የዘመቱ፣ ለወንዶችም ልብ፣ ሞራልና ወኔ አቀባዮች ነበሩ።

ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ‘ከአሜን ባሻገር’ በተሰኘ መጽሐፉ ‘ሴቶች በዋሉበት’ በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሴቶች ተጋድሎና ሚና “ከቁስ ባሻገር ከልብ ያቀርባሉ” ይላቸዋል።

“ሴቶች ባዋላጅነት ከነበራቸው የማይተናነስ ሚና በጦር ሜዳ ተጫውተዋል። እናቶቻችን በጦር ወቅት፣ መሳሪያ ያቀርቡ ነበር። ምግብ ያቀርቡ ነበር። ሃሳብ ያቀርቡ ነበር። ልብ ያቀርቡ ነበር። ደስታ ያቀርቡ ነበር። ኧረ ምኑ ቅጡ። ሴቶች ባንድ በሙቀጫ ዙሪያ፣ ማኅበረሰቡን ኬሚስት፣ ገጣሚና የፖለቲካ ተንታኝ ሆነው ማገልገላቸውን ልብ እንበል” ይላል። (ገጽ-138)

የራስ መኮንን ባለሟል የነበሩት ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማሪያም ገና በ15 ዓመት ዕድሜያቸው አድዋ ዘማች ነበሩ። "የሕይወቴ ታሪክ’  (ኦውቶባዮግራፊ) በተሰኘው ግለ ታሪካቸው ከሐረር እስከ አድዋ በዘለቀው ጉዟቸው ሴቷ (አገልጋያቸው) የነበራትን ሚና ለማብራራት ቃላት ያጥርባቸውና እንዲህ ብለው የአንባቢን ህሊና ይነካሉ።

“… ከቶ እሷ ባትኖር ኖሮ እንዴት እሆን ኖሯል! እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያደንቀኛል። ዕቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች። ከሰፈርን በኋል ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ፣ ታበላናለች። ወዲያውኑ እንዲዚህ ለማታ ታሰናዳለች። እንደዚህ የወለተ አማኑኤልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ በየሰፈሩ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል። የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት ደግሞ የበቅሎዎች አገልግሎት ይታወሰኛል። 

በመጨረሻም ድምሩን ስገምተው አድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎዎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል። ሁሉንም አያይዥ በደምሳሳው ስመለከተው የኢትዮጵያን መንግስት ነጻነቱን ጠብቀው፤ እዚህ አሁን የደረስንበት ኑሮ ያደረሱት እነዚህ የዘመቻ ሃይሎች መሆናቸውን አልስተውም። 

የኢትዮጰያ መንግስት የተባለው ተቋም፣ ላገልጋዮቹ ውለታ ምላሽ ሆኗል ወይ? የዚህን ምላሽ ለመስጠት ሳስበው እልቅ የሌለው መንገድ ይገጥመኛል። ሲሄዱ መኖር ይሆንብኛል። የማልዘልቀው እየሆነብኝ፣ እየተከዝኩ እተወዋለሁ” በማለት በቁጭት ጽፈዋል።

በርግጥም ሴቶች በኪነ-አድዋ በልካቸው ያልተዘመረላቸው፣ ‘’ደብዛዛዎቹ ጀግኖች” ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም